የ14ኛው የአአ ከተማ ዋንጫ ኮከቦች ሽልማት ዛሬ ተከናውኗል

ዛሬ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በተዘጋጀው ፕሮግራም በውድድሩ በኮከብነት ለተመረጡ እና ለተሳታፊ ክለቦች የሽልማት ስነ-ሥርዓት ተከናውኗል።

ይጀመራል ተብሎ ከተነገረው አንድ ሰዓት ከአስራ አምስት ደቂቃ አርፍዶ በተጀመረው ሥነ ስርዓት ሀብታሙ ሲሳይ (የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ)፣ ኤሊያስ ሽኩር (የኢፌዴሪ ስፓርት ኮሚሽን ኮሚሽነር)፣ ዮናስ አረጋዊ (የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር)፣ ኢሳይያስ ጂራ (የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት)፣ ኃይለሠማዕት መርሐጥበብ (የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኃላፊ) እና በርከት ያሉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሥነ ስርዓቱን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍሰሃ ውድድሩ በደመቀ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩላቸውን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። እንደ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሁሉ አቶ ዮናስ አረጋዊ እና አቶ ሀብታሙ ሲሳይ አጠር ባለ መልኩ ንግግራቸውን አድርገዋል። ከሶስቱ ግለሰቦቹ ንግግር በኋላም ለተለያዩ አካላት ሽልማት መሰጠት ተጀምሯል።

* በቅድሚያም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የየክለቦቹ (የስምንቱም ክለብ) ደጋፊዎች አስተባባሪዎች የምስክር ወረቀት ሽልማት አበርክተዋል።

* በቀጣይ የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት በለጠ ዘውዴ በውድድሩ ለተሳተፉ ስምንት ክለቦች የምስክር ወረቀት አበርክተዋል። አቶ በለጠ ከክለቦቹ በተጨማሪ በውድድሩ የተለያዩ ስራዎችን ለሰሩ ተቋማት የምስክር ወረቀት ሰተዋል።

* ሌላኛው የፌደሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ አባል እና የውድድር እና ስነስርዓት ሰብሳቢ አቶ የኔነህ በቀለ (ኢኒስፔክተር) ውድድሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የተለያዩ የፀጥታ አካላት ምስክር ወረቀት አበርክተዋል።

* በውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ሳልሃዲን ሰዒድ ከኃይለሠማዕት መርዓጥበብ የምስክር ወረቀት፣ የዋንጫ እና የ60ሺ ብር ሽልማቱን ተቀብሏል።

* ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቀውን ቡድን (ቅዱስ ጊዮርጊስ) የሚመሩት አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጂኖቭ ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሰርተፊኬት፣ የዋንጫ እና የ75 ሺ ብር ሽልማቱን ተረክቧል።

* የትናየት አበበ (ዶ/ር) የአሞሌ ተወካይ እና አቶ ኢሳይያስ ጂራ የውድድሩን ምርጥ ጎልን ሸልመዋል። ከቀረቡት ሶስት እጩዎች ( አዳነ ግርማ፣ ሳልሃዲን ሰዒድ እና ጃኮ አራፋት) ሳልሃዲን ሰዒድ ወልቂጤ ከተማ ላይ ያስቆጠረው ጎል ተመርጦ የ10ሺ፣ ሰርተፊኬት እና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

* ኮሚሽነር ዮናስ አረጋዊ የውድድሩን ኮከብ ተጨዋች ሸልመዋል። ለመጨረሻ እጩነት ከቀረቡት እጩዎች (ታደለ መንገሻ፣ ፈቱዲን ጀማል እና ሳልሃዲን ሰዒድ) የኢትዮጵያ ቡናው ፈቱዲን ጀማል ተመርጦ የ65ሺህ፣ የዋንጫ እና የምስክር ተረክቧል።

* የአዲስ አበባ እግር ኳስን በማሳደግ በሚል የተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህም መሸሻ ወልዴ (ጋዜጠኛ)፣ ጌታቸው ገብረማርያም፣ በለጥሽ ወልደማርያም (ኢንስትራክተር)፣ አስራት ኃይሌ፣ ሰዒድ ኪያር (ጋዜጠኛ)፣ አብርሃም መብራቱ፣ አሞሌ እና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

* በመጨረሻም አቶ ኤሊያስ ሽኩር፣ አቶ ዳዊት ትርፉ እና አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በውድድሩ ለተሳተፉ ክለቦች እንደየደረጃቸው የተሰላ የገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል። በዚህም በውድድሩ ከምድብ የተሰናበቱ አራት ክለቦች (ወልዋሎ ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ባህር ዳር ከተማ) ከወጪ ቀሪ ተሰልቶ (3%) 150,517.70 ብር ተሸልመዋል። ውድድሩን በአራተኝነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና 200,691.60 ብር (4%) ሲሸለም ሦስተኛ የሆነው መከላከያ 351,210.30 ብር ተቀብሏል። ከዚህ ውጪ የውድድሩ የፍፃሜ ተፋላሚ ሰበታ ከተማ 501,729.00 ብር (10%) እንዲሁም የውድድሩ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ 752,593.50 ብር (15%) ተሸልሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ