ሪፖርት | ወልቂጤዎች አስደናቂ ድልን በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ተቀዳጁ

በ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ወልቂጤን ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያልተጠበቀ የ1-0 ሽንፈትን አስተናግደው መሪነታቸውን ለፋሲል ከተማ አስረክበዋል።

የመጀመሪያውን ዙር በበላይነት ያጠናቀቁት ፈረሰኞቹ ከአዳማ ከተማ ጋር በ15ኛ ሳምንት አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ የሶስት ተጫዋቾች ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ሰልሀዲን በርጌቾ ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና ጋዲሳ መብራቴን በአሰላለፍ ውስጥ አስገብተዋል። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ከተጠቀሙበት ስብስብ ውስጥ በተከላካይ መስመር አቤኔዘር ኦቴ እና መሀመድ ሻፊ እንዲሁም አማካይ መስመር ላይ ሙሀጅር መኪን በመጀመሪያ ተመራጭነት በማስገባት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

እጅግ አሰልቺ መልክ በነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ወልቂጤ ከተማዎች በጥንቃቄ በተደረደሩ አራት ተከላካዮቻቸው ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ አጥቂዎቻቸው የሚፈልጉትን በቂ የመሮጫ ቦታ ለመከልከል ያደረጉት ጥረት ውጤታማ ነበር።

ብዙም ማራኪ ባለነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ በጣት የሚቆጠሩ የግብ ሙከራዎችን ብቻ ነበር የተመለከትነው ፤ ወልቂጤ ከተማዎች በ12ኛው ደቂቃ በሜዳው የላይኛው ክፍል ጫላ ተሺታ ከሳልሀዲን በርጌቾ እግር የነጠቀውን ኳስ ከአህመድ ጋር በጥሩ ቅብብል ከገቡ በኃላ
ጫላ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ማታሲ ሊያድንበት ችሏል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ18ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ የሜዳ ክፍል ለጌታነህ ከተከላካዮች ጀርባ ያሾለከለትን ኳስ ጌታነህ ደርሶ ከጠበበ አንግል ወደ ግብ የላኩት ኳስ ይድነቃቸው በቀላሉ ያዳነበት እንዲሁም በ39ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ዳግም እና መሐመድ በአግባቡ መግጨት ሳይችሉ የቀሩትን ኳስ ይድነቃቸው የግብ ክልሉን ለቆ በአስገራሚ ቅጥጥፍና ያመከናት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በአንፃሩ በወልቂጤዎች በኩል በ25ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ጫላ አፈትልኮ ገብቶ ከመጠቀሙ በፊት ማታሲ ያዳነበት ሌላኛው የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራ ነው።

በእረፍት ሰዓት በቅርቡ የተከበረውን የዓድዋ ድል በማስመልከት ወደ ስፍራው በእግር ተጉዘው የተመለሱትን ሁለት እንስት የክለቡ ደጋፊዎችን የእውቅና ስጦታና ማስታወሻ በክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ አብነት ገ/መስቀል ሊበረከትላቸው ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልቂጤዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በ52ኛው ደቂቃ በጊዮርጊስ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ ወጣቱ የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታ ኳሱን ይዞ በመግባት በግራ እግሩ በመምታት ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በአንፃሩ ባስተናገዱት ግብ ጫና ውስጥ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተከላካይ ቁጥራቸውን በመቀነስ በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

በወልቂጤ የሜዳ አጋማሽ አድሎቶ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ጊዮርጊሶች በቂ የሆኑ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ ሀይደር ሸረፋ ከሳጥን ጠርዝ የሞከራት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ሰልሀዲን ሰኢድ በቅጣት ምት እና በጨዋታ ያደረጋቸው ሙከራዎች አስቆጭ ነበሩ።

በሁለቱም አጋማሾች በተሻለ ጠቅጠቅ ብለው በመከላከል የተዋጣላቸው የነበሩት ወልቂጤዎች ጨዋታውን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከባድ አድርገውባቸው ተስተውሏል። በተጨማሪም ባለ በሌለ ኃይል ለማጥቃት ሲታትሩ ከነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጀርባ በሚፈጠሩት ክፍት ቦታዎችን ወልቂጤዎች በተለይ ለአህመድ ሁሴንና ጫላ ተሺታ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል እንዲጠቀሙ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።

በዚህም ሒደት ጫላ ተሺታ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም አህመድ ሁሴን በሶስት አጋጣሚዎች እጅግ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በማይታመን መልኩ ሲያመክኗቸው ተስተውሏል። ወልቂጤዎችም ያገኛትን አንድ ግብ አስጠብቀው ነጥባቸውን ወደ 22 በማሳደግ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነበሩበት ነጥብ ረግተው ወደ ሶስተኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ