የፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ከአሰልጣኞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን እንዲህ አጠናቅረናቸዋል።

👉 ሲሳይ አብርሃም እና ከፊቱ የተደቀነው ፈተና

ከቀናት በፊት ከአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ጋር የተለያዩት ስሐል ሽረዎች ባሳለፍነው ዓርብ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃምን በዋና አሰልጣኝነት መቅጠራቸው ይታወሳል።

ከአዲሱ ሹመታቸው ማግስት ቡድኑ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በኢትዮጵያ ቡና አሰቃቂ የሆነ የ6-1 ሽንፈት አስተናግዷል። በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉት አሰልጣኙ በቀጣይ አዲስ የተረከቡትን ቡድን ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ብዙ የቤት ስራ እንደሚጠብቃቸው ያሳየ ጨዋታም ሆኗል።

በተለይ በተለይ ከሁሉም በላይ የአሰልጣኙ የመጀመሪያ ፈተና የሚሆነው በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ በደምብ እንደታየው የቡድኑ የመከላከል አወቃቀር ከፍ ያለ አፅንኦት ተሰጥቶ ሊፈተሽ ይገባል። በሀገራችን እግርኳስ አውድ አንፃር ማጥቃት እንቅስቃሴ በግላዊ የተጫዋቾች ብቃት የሚወሰን እንዲሁም መከላከል ደግሞ ለተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች የመተው የተሳሳተ አመለካከት ቢኖርም ስሑል ሽረ ግን እንደ ቡድን የመከላከል ሒደታቸው እጅግ የተዳከመ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል።

እንደ ቡድን ኢትዮጵያ ቡናን በላይኛው የሜዳ ክፍል ማፈንን አስቦ ወደ ሜዳ የገባው ቡድኑ በሜዳው የላይኛው ክፍል አምስት ተጫዋቾች የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ምስረታ ለማቋረጥ ባልተደረጃ መልኩ በግለሰቦች አነሳሽት ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ አልነበሩም። በተጨማሪም ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ ለመከላከል ከሚጥረው የተከላካይ መስመር ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ተጋጣሚያቸውን የደቀነባቸውን ስጋት ለመቋቋም ሲቸገሩ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቡና አጥቂ መስመር ተጫዋቾች ፍጥነት አንፃር የቡድኑ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች መቋቋም ተቸግረው እንኳን ቡድኑ የጨዋታ እቅዱን አለመከለሱ ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍለው ተስተውሏል።

ሌላኛው የቡድኑ የመከላከል ችግር የነበረው ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በመከላከሉ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ እጅግ ደካማ መሆን ነው። በመስመሮች መካከል የሚፈጠሩ የተጋነኑ ክፍተቶች፣ የኃላ አራት ተከላካይ መስመር ተጫዋቾች እጅግ የጠበበ አቋቋም ከብዙ በጥቂቱ የቡድኑን የመከላከል አወቃቀር ችግር ነፀብራቆች ናቸው።

አሰልጣኝ ሲሳይ ይህን የመከላከል መወቅር ችግር በፍጥነት በመፍታት ቡድኑን ከዚህ አስከፊ ሽንፈት በፍጥነት እንዲነቃ የማድረግ የቤት ስራን አንግበው ስል የማጥቃት ኃይል ካለው ሲዳማ ቡና ጋር ለመጫወት ቀጣዩን ዓርብ ይጠባበቃሉ።

👉 የጊዜያዊ አሰልጣኞች ፍልሚያ

በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ የተጫወቱት ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማን እየመሩ ወደ ሜዳ የገቡት ጊዜያዊ አሰልጣኞቹ ፍስሀ ጥዑመልሳን እና ብርሀኑ ወርቁ ነበሩ። አሰልጣኝ ፍስሀ አራተኛ ጨዋታውን አድርጎ ጣፋጭ ድል ሲቀዳጅ አሰልጣኝ ብርሀኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝነቱን በሽንፈት ጀምሯል።

👉 ያልተፈታው የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር እንቆቅልሽ

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን በማሳየት የመጀመሪያውን ዙር ሊጉን በመምራት ቢያጠናቅቁም ትናንት በወልቂጤ ከተማ በደረሰባቸው ሽንፈት መሪነታቸውን ለፋሲል ከተማ አስረክበው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ለመንሸራተት ተገደዋል። ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ በሜዳቸው ሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ ከተቸገረው ቡድኑ በስተጀርባ ያልተፈታው የፊት መስመር እንቆቅልሽ ከፍ ያለ ድርሻን የሚወስድ ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በስብስቡ ውስጥ በሀገራችን ደረጃ በትውልዶች መካከል ድንገት ብቅ ያሉትን ሁለቱን እጅግ ምርጥ አጥቂዎችን ቢይዝም ሁለቱን አጥቂዎች በጋራ ለመጠቀም በክለቡ የተደረጉ ጥረቶች እስካሁን አመርቂ የሚባል ውጤት ማስገኘት አልቻሉም።

በመጀመሪያው ዙር በተለይ ከ10ኛው ሳምንት ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ4-3-3/4-2-3-1 አደራደር ጌታነህ ከበደን በፊት አጥቂነት በተጠቀሙባቸው ጨዋታዎች ከአቤል ያለውና ጋዲሳ መብራቴ ጋር ግሩም ተግባቦቶ በመፍጠር ለቡድኑ ወሳኝ ነጥቦችን ሲያስገኙ ተስተውሏል ፤ በዚህም አጨዋወት ውስጥ ጌታነህ ከበደ ወደ መሀል እየተሳበ ለሌሎች የቡድን አጋሮቹ ቀርቦ ኳሶችን ሲቀባበል እንዲሁም ለሌሎች ተጫዋቾች የመሮጫ ቦታን ከመፍጠር በዘለለ ወደ መስመሮችም በመውጣት ተገማች ባልሆነ እንቅስቃሴ የቡድኑ የማጥቃት ሒደትን ከፍ ባለ ትጋት ሲመራ ቆይቷል።

ነገርግን ሰልሀዲን ሰዒድ ከጉዳት ማገገሙን ተከትሎ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጅኖቨ ከ14ኛው ሳምንት የፋሲል ከተማ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ ሰልሀዲን ሰዒድን ወደ ቋሚነት ለመመለስ ሲባል በቀደመው አደራደር ሰልሀዲንን ከፊት በማድረግ ጌታነህ ከበደ ከአጥቂ ጀርባ በ10 ቁጥር ሚና እንዲጫወት ያስገደደ ነበር። ይህም የሰልሀዲን መመለስ ቡድኑ ፊት ላይ የነበረውን የመታተር ደረጃ በእጅጉ ያወረደው ሲሆን ሰልሀዲን ሰዒድ ሜዳ ላይ በገባባቸው ደቂቃዎች ሁሉ ቡድኑ ቀጥተኛ አጨዋወት ለመተግበር ሲሞክር ተስተውሏል። ይህም በአዳማው ጨዋታ ምን ያህል ውጤታማ እንዳልነበር እና በትላንቱም ጨዋታ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባበት ወዲህ መሰል የቀጥተኛ አጨዋወት ዝንባሌዎችን አስተውለናል።

ይህ ለቡድኑ ውጤት ማጣት አንዱ ምክንያት ሲሆን እየተስተዋለ ይገኛል። ምንም እንኳን ሰልሀዲን ሰዒድ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ቢሆንም ቡድኑ ጥሩ ግቦችን ሲያመርትለት በነበረው የፊት መስመር ላይ አላስፈላጊ የቅርፅና የአጨዋወት ለውጥ ማድረግ መሞከሩ ቡድኑን እየጎዳው ይመስላል። በቀጣይም የአጥቂ ክፍል ጥምረቱን ስኬታማ ማድረግ የአሰልጣኙ ከባድ የቤት ስራ ይሆናል።

👉 የወልቂጤ ከተማ የመከለካል አደረጃጀት

በሊጉ ጠንካራ የመከላከል ክብረወሰን ካላቸው ግንባር ቀደም ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወልቂጤ በጉዳት ከኃላ መስመሩ ከሚጠቀምባቸው አራት ተጫዋቾች ሶስቱን ወሳኝ ተጫዋቾችን ቢያጣም በትላንቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የቀደመውን የመከላከል ጥንካሬውን በማስቀጠል ግብ ሳያስተናግድ መውጣት ችሏል።

ቡድኑ በትላንቱ ጨዋታ ሦስቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የሚፈልጉትን ጥልቀት እንዳያገኙ አራቱ ተከላካዮች በትይዩ በመገኘት በአብዛኛው የጨዋታ ሒደቶች በተናበበ መልኩ በጋራ ወደ ፊት እና ወደ ኃላ እየተሳቡ በመንቀሳቀስ ጨዋታውን ለጊዮርጊስ ፈታኝ ማድረግ ችለዋል።

ከእነሱ ፊት የነበሩት አማካዮች (በረከት ጥጋቡና አልሳሪ አልመህዲ) በተለይ ለተከላካዮች ቀርበው በቂ የመከላከል ሽፋን ከመስጠታቸው በዘለለ ከአህመድ ሁሴን ውጭ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ተጠቅጥቀው ሲከላከሉበት የነበረው መንገድ ለአሰልጣኙ አድናቆት የሚያስቸራቸው ነው።

👉ዓበይት አስተያየቶች

🗣 ሥዩም ከበደ የአሰላለፍ ለውጥ በማድረግ ስለተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች?

“አዲስ ተጨዋች አልተጠቀምንም። ሙሉ ለሙሉ የነበሩት ተጨዋቾች ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ አብረውን የነበሩ ናቸው። ቋሚ የመሆን እድል ስላላገኙ ነው እንጂ አብረውን የነበሩ ናቸው። ኪሩቤልም የበለጠ የራስ መተማመን ኖሮት እንዲጫወት ነው ያደረግነው። በተጨማሪም ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ እድል ሳያገኝ ቆይቶ ነበር። ነገር ግን የሳማኬን በጊዜው አለመገኘት ተከትሎ ዛሬ ዕድሉን በአግባቡ ተጠቅሟል። ሳማኬም ሲመለስ ይህ ግብ ጠባቂ እስካልተበላሸበት ጊዜ ድረስ ቁጭ ብሎ ይጠብቃል ማለት ነው። ቴዎድሮስ ላይ እያየን ያለነው በጎ ነገሮችን ነው።”

🗣የአዳማው ምክትል አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በፋሲሉ ጨዋታ ስለነበረው የዳኝነት ችግር እና ቀጣይ የቡድኑ የሁለተኛ ዙር እንቅስቃሴ

“በመጀመሪያ አስበን የመጣነው 3 ነጥብ ይዞ ለመሄድ ነበር። ነገር ግን ዳኛው ያሰብነውን እንዳናሳካ አድርጎናል። ትክክለኛ ውሳኔዎች ሜዳ ላይ ሲወሰኑ አልነበረም። ይህ ደግሞ ተጨዋቾቻችን ተረጋግተው እንዳይጫወቱ አድርጎታል። በአጠቃላይ በዳኝነት ስህተት ምክንያት ጭቅጭቆች የበዙበት ጨዋታ ነበር። እኛ ዛሬ ዳኛን ነው የገጠምነው። በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን በሁለተኛው አጋማሽ እኛ ተጭነን ተጫውተናል።”

“በሁለተኛ ዙር የተሻለ ነገር ይኖረናል ብለን እናስባለን። እኛ ከ1-3ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ነገር ግን ይህ የሚሆነው አስተዳደራዊ ችግሮቻችን ከተቀረፉ ነው። ይህ ቡድን በደንብ አቅም ያለው ስለሆነ ከ1-3 ሆነ መጨረስ በትክክል ይችላል። ግን እንደገለፅኩት የእኛ የበላይ ሰዎች ቡድኑ ውስጥ ያለውን የደሞዝ ችግር በቶሎ መፍታት ከቻሉ ነው።”

🗣ካሳዬ አራጌ ስለ ሽረው አስደናቂ ድልና ቀጣይ እቅድ

” ጨዋታው ከውጤት አንፃር ጥሩ ነው ፤ ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር ችለናል። ነገር ግን በቀላሉ አንዳንድ እንቅስቃሴው ሊቀጥልባቸው የሚችሉ ኳሶች በቀላሉ ይበላሹ ነበር። ነፃ ቦታዎች ላይ ኳሱን በደንብ እንቆጣጠር ነበር። ነገርግን አንዳንዴ የተጋጣሚ ተጫዋቾች በበዛባቸው አካባቢዎቹ ኳሱን መቆጣጠር እየቻልን በቀላሉ ኳሶች ይበላሹ ነበር። በመጀመሪያው ዙር ላይ ከጨዋታ ጨዋታ እንደምናደርገው በተለይ ሒደቱ ላይ ያሉ ጨዋታውን ከተቆጣጠርን ማሸነፍ እንችላለን የሚል እምነት ስላለን በዛ ውስጥ የሚታዩትን ስህተቶች እያረምን ለመሄድ እንሞክራለን።”

🗣 የባህርዳሩ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድኑ በርከት ያሉ እድሎችን ስላመከነበት ምክንያት

“መጀመሪያ ደስ ያለኝ ነገር እነዛን የጎል እድሎች መፍጠር መቻላችን ነው። የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ በተደጋጋሚ ለመድረስ ሞክረናል። ነገር ግን ለማመን የሚከብዱ ኳሶችን አምክነናል። በተለይ ከውሳኔ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ስህተቶች ነበሩብን። አንዳንድ ጊዜ የቀንም ጉዳይ ነው። አንድ ቀን ሁለት እና ሶስት ጎል ልታገባ ትችላለክ አንዳንዴ ደግሞ አይሳካም። ሆነም ቀረ ይህንን ነገር እኛ በዛሬው ጨዋታ ያሳየነው ደካማ ጎን አድርገን እንወስደዋለን። አጥቂያችን ስንታየሁ ብዙ ኳስ አምክኗል። ነገር ግን ወጣት ስለሆነ ይማራል። እንደ አሰልጣኝ ነገ ብሄራዊ ቡድን ይደርሳል ብዬ የምጠብቀው ተጨዋች ነው።”

🗣 አሰልጣኝ ጳውሎስ በቀድሞ ክለቡ ስለተደረገለት መልካም አቀባበል

“ጥሩ መስራት መልካም ነው። ጥሩ መስራት ለእራስ ነው። ሁል ጊዜ በሙያህ ታማኝ ከሆንክ ታሪክ ያስታውስሃል። ባህር ዳር እያለሁ እንደ ግርማ ዲሳሳ አይነት ተጨዋቾችን ማውጣቴን ሳይ ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ። ዛሬ ያየኋቸው ተጨዋቾች በአብዛኞቹ የራሴ ስለሆኑ ኩራቴ ነው።”

🗣 የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጅኖቨ በደጋፊዎች ዘንድ ስለነበረው ተቃውሞ

” ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀገሪቱ ምርጥ ክለብ እንደመሆኑ ከደጋፊዎች ሆነ ከሌሎች አካላት ሁሌም ጫና ያለበት ቡድን እንደሆነ እረዳለሁ። ነገርግን አንዳንድ ጊዜ የደጋፊዎች ጥያቄ መጥፎም ተጫውተን ስናሸንፍም ደስተኛ አይደሉም። መጥፎ ተጫውተን ሳናሸንፍ ስንቀርም አሁንም ደስተኛ አይደሉም። ደጋፊዎች ሁሌም ስንሸነፍ ደስተኛ አይደሉም፤ ይህ የተለመደ ነገር ነው። ነገርግን አንዳንዴ ጥሩ ተጫውተህ ትሸነፋለህ። በዛሬው ጨዋታ ቁጥሮች ቢኖሩ ኖሮ ከ60% በላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነበረን። በተጨማሪም 8(9) ተጫዋቾች ከኳስ ጀርባ አድርጎ ከሚጫወት ቡድን ላይ ጎል ማስቆጠር እጅግ ከባድ ነው። ”

🗣ደግአረግ ይግዛው ብዙ እድሎችን ስለሚያበክነው የወልቂጤ የፊት መስመር

” በልጆቻችን ላይ ከፍተኛ ጉጉትና የልምድ ማነስ ይታያል። ነገርግን እኛ እንደ ቡድን ትኩረት የምናደርገው የነበራቸው እንቅስቃሴ እና ለማሸነፍ የነበራቸውን ቁርጠኝነት ነው። ይህን እኛ ትልቅ ቦታ እንሰጣቸዋለን። ጎል ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች አሉ። በቀጣይም የሚቀሩትን ነገሮች ለማሻሻል እንሰራለን። አሁን ላይ እየሄድንበት ያለው መንገድ ጤናማ ነው ብዬ አስባለሁ። ቀጣይ ሁለተኛው ዙር ከመጀመርያው የበለጠ በአካልም በአዕምሮ ዝግጅት የሚፈልግ ስለሆነ የተሻለ ስራ መስራት ይኖርብናል።”

🗣 አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም በአጋማሹ ስላደረጓቸው ዝውውሮች

“ባሉን ክፍተቶች ላይ ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾች አምጥተን ቡድኑ ውስጥ አካተናል። ሁለት ተጫዋቾች በቅርቡ ይካተታሉ። ፎፋና የነበረውን የወረቀት ሁኔታዎችን ጨርሷል። ተስፋዬ አለባቸው እዚህ ከመጣ በኋላ ታሞ ነው ያልገባው። ሙሉ የቡድን ስብስባችንን ስናገኝ ወደ ጥሩ አቋም እንመለሳለን። እግርኳስ ነው ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም። ደጋፊዎቻችን በተቻለ አቅም ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል። ከድክመቶቻችን ተነስተን በቀሪ ጨዋታዎች በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ጥረት እናደርጋለን።”

🗣ዘርዓይ ሙሉ ተሻሽሏል ስላሉት የቡድናቸው የተከላካይ ክፍል

“የመከላከል ችግራችን ዛሬ ላይ የለም። ለምሳሌ የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር የመሳይ በረኛው አቋቋም ነው ነው። ስለዚህ የተከላካይ ስህተት አንለውም። ሁለተኛውም መግባት ስላለበት ነው የገባው፡፡ ሜዳህ ላይ ስትጫወት አጥቅተህ ነው የምትጫወተው። ከሜዳ ውጪ ስንጫወት ግን የመስመር አጥቂዎች ተመልሰው ተከላካዩን አግዘው እንዲጫወቱ ማድረግ እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ ግን አንደኛ ዙር ላይ በነበረው አይደለም ግቦች የተቆጠሩብን። ይሄ ደግሞ የሚቀረፍ ስለሆነ እናስተካክላለን፡፡”

🗣አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስለ ዝውውር እቅዳቸው

“በኛ ሀገር ሁኔታ በዚህ ወቅት ተጫዋች ለማዘዋወር ሁኔታው አይፈቅድልህም። ተጫዋች ላምጣ ብትልም እንኳን በስብስብህ ካሉ የተሻሉ ተጫዋቾች ለማግኘት ትቸገራለህ። አንድ ተጫዋች ለማምጣት ዕድል ሊኖረን ይችላሌ ከዛ ውጭ ባለን ስብስብ ነው የምንቀጥለው።”

🗣አዲሱ የወልዋሎ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ስለቡድኑ የመከላከል ድክመትን ለመፍታት ስላሰበው ነገር እንዲሁም ስለቡድኑ አጨዋወት

“በውድድር አጋማሽ ስትመጣ ውድድር ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ማግኘት ይቸግራል። አብዛኞቹ ብዙ ያረፉ ናቸው፤ ስጋት ነበረኝ። የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃ ላይ የአካል ብቃት ችግር ይታዩ ነበር። እነዚን በተደጋጋሚ ልምምድ አሻሽለን በቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ቡድን ይዘን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን። በሁለት ቀን ውስጥ የተለየ አጨዋወት ፈጥሬ ቡድኑን ሌላ ውዥንብር ውስጥ መክተት አልፈለግኩም። የተወሰነ ጥገና ለማድረግ ሞክሬያለው እንጂ ቡድኑ በዚ መንገድ እንዲወጫት አልፈልግም።”


©ሶከር ኢትዮጵያ