“የኢትዮዽያ እግርኳስን ታሪክ የቀየረ ወርቃማው ጎል” ትውስታ በሳላዲን ሰዒድ አንደበት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተቀላቀለበትን ወሳኝ ጎል ያስቆጠረው ሳላዲን ሰዒድ የትውስታ አምዳችን የዛሬ እንግዳ ነው።

ወደ 2013 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው ዙር የተገናኙት ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በኦምዱርማን ባደረጉት ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተገኙ ሁለት አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምቶች ሱዳን 5-3 በማሸነፍ ነበር የመልሱን ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ የተዘጋጁት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለት እና ከዛ በላይ ንፁህ ጎሎች ማሸነፍ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞውን ያረጋግጥለታል። ይህ ወርቃማ ዕድልን ለመጠቀም የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ከሚያደርጉት ጠንካራ ዝግጅት በተጓዳኝ ፌዴሬሽኑ፣ ባለሀብቶች ብሔራዊ ቡድኑን ለማነቃቃት ከፍተኛ ሽልማት እንደሚያበረክቱ ቃል እየገቡ ነው። ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያሳልፈው የመጨረሻው ምዕራፍ ደርሶ እሁድ ጥቅምት 4 ቀን 2004 በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሚካሄደው ወሳኝ ጨዋታ ከእኩለ ለሊት ጀምሮ በስቴዲየሙ ዙርያ በርካታ ተመልካች መሠለፍ ጀምሯል።

ጨዋታው ተጀምሮ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል መጠናቀቁ እና ቡድኑ ግልፅ የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ ለመፍጠር መቸገሩ በስታዲየሙ የተገኘው እና በቤቱ ሆኖ በቴሌቭዥን የሚከታለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካችን አስጨንቋል። በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው በመግባት ተጋድሎ ያደረጉት ዋልያዎቹ ከእረፍት መልስ በአዳነ ግርማ ጎል ቀዳሚ መሆን ቻሉ። በዚህች ጎል የተነቃቁት ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የግድ አንድ ተጨማሪ ጎል ያስፈልግ ነበር። በዚህ ሰዓት ነው ወርቃማ ጎሏን ሳላዲን ሰዒድ አስቆጥሮ በድምር ውጤት 5-5 ቢሆኑም ከሜዳ ውጭ ብዙ ባስቀጠረ ሕግ ኢትዮጵያ ከ31ዓመት በኃላ ወደ መሰረተችው አፍሪካ ዋንጫ ለ10ኛ ጊዜ በመሳተፍ ዳግም መመለስ የቻለችው። ይህች ጎል የኢትዮጵያ እግርኳስን በብዙ መንገድ አነቃቅታለች፣ ከሜዳ የራቀውን ተመልካች ወደ ሜዳ መልሳለች፣ ለኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በውጪ ሀገራት የመጫወት ዕድል እንዲያገኙ አስችላለች፣ እግርኳሱም ትኩረት እንዲያገኝ አግዛለች። ይህችን አይረሴ ጎል ያስቆጠረው ሳለዲን ሰኢድ በትውስታ ዓምዳችን ወደ ኃላ ተመልሶ ጊዜውን እንዲህ ያስታውሰዋል።

” በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በሁሉም ዘንድ የማይረሳ ትውስታ ነው። በእግርኳስ ህይወቴ እጅግ የተደሰትኩበት ትልቅ ቦታ የምሰጠው ታሪካዊ ቀን ነው። አሁን ከኮረና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ውድድሮች በመሠረዛቸው ሁላችንም ቤት የምንቀመጥበት ጊዜ ነው። ይገርምሀል ያን ጊዜ የሚያስታውሰውን ቪዲዮ ከቤተሰቦቼ ጋር ሆነን ስናየው የሚሰማኝ ስሜት ቀላል አይደለም። ለአንተ ሳወራህ አቅልዬ ላወራህ እችላለሁ። እኔ ውስጥ ያለው ስሜት ግን በየትኛውም ቋንቋ የማይገለፅ ነው። ለልጆቼ ለቤተሰቦቼ የማወርሰው፣ የምናገረው አንድ ታሪክ በመኖሩ ደስተኛ ነኝ። ይህች በሁላችንም እግርኳስ ተጫዋቾች ዘንድ ሁሉን ነገር ማድረግ እንችላለን የሚል የይቻላል መንፈስ የፈጠረች ጎል ናት።

በሙገር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስኬታማ ቆይታ አድርጎ ከስድስት ዓመታት የግብፅ፣ አልጄርያ እና ቤልጅየም ቆይታው በኋላ በ2008 ዳግመኛ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው አንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ከጉዳት ጋር እየታገለ አሁንም የሊጉ አስፈሪ አጥቂ መሆኑን እያሳየ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ