“አስታውሰውኝ ይህን ድጋፍ ስላደረጉልኝ በጣም አመሰግናለሁ” ሳምሶን ሺፈራው (ጆሮ)

ለኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው የመስመር አጥቂው ሳምሶን ሽፈራው (ጆሮ) የመኪና ስጦታ ተበረከተለት።

የብዙዎች እግርኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ በሆነችው መሳለሚያ (ኳስሜዳ) ለተወለደው የቀድሞ ድንቅ የመስመር አጥቂ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን ላበረከተው አስተዋፆኦ እውቅና በመስጠት ነው የመኪናውን ስጦታ ያበረከቱለት። ይህን በጎ አላማ በማስተባበር ድጋፍ ያደረጉለት ቴዎድሮስ ብርሀኑ (ባርያው)፣ ሰይፈ ውብሸት፣ መላኩ (የጊዮርጊስ ደጋፊ) ሲሆኑ ከአሜሪካ የቀድሞ ተጫዋቾች ብሩክ እስጢፋኖስ (ካንቶና )፣ ዳዊት አስመላሽ እና እሱባለው ኦሜጋ ሌሎችም በዚህ በጎ ተግባር ተሳትፈዋል።

ይህን መልካም ተግባር በማስተባበር ላይ የነበረው ቴዎድሮስ ብርሀኑ ያነሳሳቸውን ምክንያት ሲናገር ” ይህ በጎ ተግባር የመጀመርያ አይደለም። በተለያየ ጊዜ የቀድሞ ተጫዋቾችን በሀገር ውስጥም በውጭ ያሉትን በማስተባበር ስናስታውስ ቆይተናል። ዛሬ ለሳምሶን ያደረግነው ድጋፍ ህይወቱን እንዲቀይር እና የቀድሞ ባለውለተኞች እንዳይቸገሩ በማሰብ ነው። እንደሚታወቀው የቀድሞ ተጫዋቾች ምንም ያልተጠቀሙ፣ ምንም ገቢ የሌላቸው በመሆናቸው ይህን አስተባብረን ለማድረግ ችለናል። በቀጣይም እነዚህን የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታዎችን ለመደገፍ አስበናል።” ብሏል።

የቀድሞ ተጫዋች ሳምሶም ሽፈራው (ጆሮ) ስለተደረገለት ድጋፍ እንዲህ ብሏል። “አስታውሰውኝ ይህን ድጋፍ ስላደረጉልኝ በጣም አመሰግናለሁ። ያልጠበኩት ምንም ሳላውቅ ጠርተውኝ ይህን መኪና ሲሰጡኝ በጣም ነው የደነገጥኩት። ቀድሞ በክለብ በብሔራዊ ቡድን አብረውኝ የተጫወቱት እሱባለው ኦሜጋ፣ መስፍን ጫንቃ፣ ቢንያም፣ ኢንጅነር በኃይሉ ፣ ብሩክ (ካንቶና)፣ ዳዊት አስመለሽ እንዲሁም እዚህ ያሉትን መርካቶ አካባቢ ያሉ እነ መላኩን፣ መኮንን ፣ በተጨማሪም ቴዎድሮስ (ባርያው) ስማቸውን የዘነጋሁትን በሙሉ እኔን እንዳሰቡኝ ፈጣሪ እነርሱንም ያስባቸው። ” ብሏል።

ለኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ሳምሶን ሽፈራውን የእግርኳስ ህይወት አስመልክቶ በቀጣይ ሰፊ ዘገባ ይዘን የምንመለስ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ