አምሀ በለጠ የት ይገኛል ?

በሐረር ቢራ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ንግድ ባንክ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የተጫወተው አማካዩ አምሀ በለጠ በተለይ በሐረር ቢራ እና ሲዳማ ቡና ጥሩ ጊዜን አሳልፏል፡፡ ከድሬዳዋ ከተማ ከለቀቀ በኋላ ወደ ሲዳማ ቡና አምርቶ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከሊጉ ራቅ ያለው አምሀ አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ አውርቶናል።

እግር ኳስን የጀመረው ተወልዶ ባደገባት ሐረር ከተማ ውስጥ ነው፡፡ 1990ዎቹ ጅማሬ ላይ በፕሮጀክት በመታቀፍ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ተጫዋቹ በመቀጠል በትምህርት ቤት ውድድሮች ሐረር እና አካባቢዋን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች በመወከል በመጫወት አሳልፏል፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አመሀ ከብዙሀኑ የሀገራችን የእግር ኳስ አፍቃሪ ዘንድ የተዋወቀው በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ በተቀላቀለው በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ይሰለጥን በነበረው ሐረር ቢራ ውስጥ ነበር፡፡

በሐረር ቢራ ቆይታው ረዘም ያለን ጊዜ ቡድኑን በአማካይ ስፍራ ተሰልፎ ከማገልገል ጀምሮ እስከ አምበልነት ድረስ ዘልቋል፡፡ ረዘም ያለ ጊዜን በትውልድ ስፍራው ክለብ መጫወት የቻለው ይህ አማካይ በ2003 እና 2004 በሐረር ቢራ ቆይታው በሜዳ ላይ የነበረው አስደናቂ ብቃት የማይረሳ ነበር። ከመሀል ሜዳ እየተነሳም በርካታ ግቦችን ሲያስቆጥር እንደነበረም ይታወሳል፡፡ ከሐረር ቢራ ከለቀቀ በኃላ አዳማ ከተማን በመቀላቀል ክለቡ ከአንደኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ጥሩ አገልግሎት መስጠት የቻለ ሲሆን በሊጉም አዳማ ባደገበት ዓመት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ እንዲያጠናቅቅ በመርዳት ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን መልካም የውድድር ዓመትን አሳልፏል፡፡

አዳማ ከተማን ከለቀቀ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢያመራም በጉዳት የተጠበቀውን እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችል ቀርቶ አንድ ዓመት ከግማሽ ከቆየ በኃላ ወደ ድሬዳዋ ከተማ አንርቶ 2009 ላይ ቡድኑ ላለመውረድ ሲጫወት እንዲተርፍ ካደረጉ ተጫዋቾች መሀካል አንዱ ሆኖ ነበር። በድሬዳዋ በሰዓቱ ባሳየው መልካም ግን አጭር ቆይታ የተነሳ 2010 ላይ ሁለት ዓመት ወደ ሲዳማ ቡና አምርቶ በገባበት ዓመት ሲዳማን በሚገባ ማገልገል ችሏል፡፡ በሲዳማ ቡና አንድ አመት የተሳካ ጊዜን ቢያሳልፍም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ግን ከሜዳ ርቆ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያም ተጫዋቹ በምን ምክንያት ከእግር ኳሱ እንደራቀ አግኝታ ጠይቃዋለች።

“በሲዳማ ቡና የነበረኝ ጊዜ የሚረሳ አልነበረም። ለኔ የነበራቸው ነገርም ጥሩ ነበር። ስራ አስኪያጁ መንግስቱም ሆኑ አሰልጣኞቹ ዓለማየሁ እና ዘርዓይ ጥሩዎች ነበሩ፡፡ በቡድኑ እየተጫወትኩ እያለ አባቴ ታመመ እና እሱን ለማሳከም ወደ ሐረር ሄድኩኝ። ያን እያደረኩ እያለ በሰዓቱ ድሬዳዋ አጣብቂኝ ውስጥም ነበር እና ስመዖን አባይ እና አምበሉ ሳምሶን አሰፋ በተደጋጋሚ ይደውሉልኝ ነበር። ድሬዳዋ እንድመለስ በጣምም ይጨቀጭቁኝ ነበር። እኔ ደግሞ ሲዳማ ቡናን ወድጄው ነበር ፤ ተጫዋቾቹም አመራሮቹም ለኔ መልካም ነበሩ፡፡ ኑሮዬንም እዛው አድርጌ ነበር ፤ አግብቼ ሀዋሳ ነበር የተዳርኩት ሴንትራል ሆቴል ፤ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር። ከሌሎች ክለቦች የወደድኩት ክለብም ነበር። ነፃነት አለ ፤ ብዙ በጣም ወድጄው ነበር። አባቴ ህመሙ ስለበርታበት ከጎኑም ልሁን ብዬ በማሰብ ነበር ወደ ሐረር የሄድኩት። ሆኖም ስምዖን እና ሳሚም ከድሬዳዋ እየደወሉልኝ ስለነበር እናቴን አማከርኳት። ‘ሲዳማ ቡና ተመልሰህ ከምትሄድ እዚሁ ቅረብ ይሻላል’ አለችኝ። ሲዳማ ቡና ቀሪ ውል ስለነበረኝ መንግስቱ ኃላፊውን ስለማከብረው መቅረብ ትንሽ ፈራሁ። እናቴን ይዤ ከሀረር ሀዋሳ ሄጄ ‘አንቺ አውሪው’ ብያት እሷም አስረድታው እያዘነ ‘ለአንቺ ስል ነው መልቀቂያውን የምሰጠው’ አለ። መልቀቂያንም ሰጠኝ። ከሰጠኝ በኃላ ግን ለድሬዳዋዎች ‘ጨርሻለሁ ወስጃለሁ’ ብዬ ስደውልላቸው ጥሩ ምላሽ አልሰጡኝም። ለምን እንደሆነ ግራ ገብቶኛል በሰዓቱ መልስ አጥቻለው። ምን እንዳሰቡ አላውቅም። ከምወደው ክለብ መጥቼ ልጫወት ብልም ስልክ እያነሱም ነበር።

“ኮሮና መጣና ጊዜው መጥፎ ሆነ እንጂ አንድ ክለብ ለመጫወት እየተዘጋጀውኝ ነበር፡፡ ሙከራ እንዳደርግ ቃል የገቡልኝ ነበሩ። እኔም ጥሩ ተዘጋጅቼ ነበር። ከፈጣሪ ጋር ግን መመለሴ አይቀርም። ወደ እግር ኳሱ በድጋሚ እመለሳለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ