የዘመናችን ክዋክብት ገፅ | ከኤርሚያስ ኃይሉ ጋር …

የጅማ አባ ጅፋሩ የመስመር አጥቂ ኤርምያስ ኃይሉ የዛሬው የዘመናችን ክዋክብት ገፅ እንግዳችን ሲሆን ጊዜውን በምን እያሳለፈ እንደሆነ በአዝናኝ ጥያቄዎች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ባለፉት ዓመታት በመስመር አጥቂነታቸው አስጨናቂ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ኤርምያስ ኃይሉ በዘመናችን ክዋክብት ገፅ የዛሬ እንግዳችን ነው። ኤርሚያስ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ መርካቶ ሲሆን እግርኳስን የጀመረው ሰፈር ውስጥ በሚገኝ ጨፌ የተሰኘ ሜዳ ሻምበል በሚባል ፕሮጀክት 1998 አካባቢ ነበር ። በመቀጠል ወደ ኒያላ ታዳጊ ቡድን ያመራው ኤርምያስ ኃይሉ በኒያላ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ጥሩ ጊዜን አሳልፎ በ2006 ወደ ዳሽን ቢራ በማምራት ዳሽን ቢራ እስከ ፈረሰበት ጊዜ ክለቡን ማገልገል ችሏል። ኤርሚያስ 2009 ላይ አዲስ አዳጊውን ፋሲል ከነማን ተቀላቅሎ በክለቡ የሁለት ዓመታትን ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ጅማ አባ ጅፋር በማምራት ግማሽ ዓመት ቆይቶ ድሬድዋን የተቀላቀለ ቢሆንም በድጋሜ ወደ አባ ጅፋር ተመልሶ ፕሪምየር ሊጉ በኮሮና ምክንያት እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በጅማ መለያ ሲጫወት መቆየቱ የሚታወስ ነው። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ጋር በቀጣዮቹ ጥያቄዎች ያደረግነውን ቆይታ እነሆ…

ጊዜህን እንዴት ነው የምታሳልፈው ?

ልምምድ አላቆምኩም ፤ ጠዋት ጠዋት ሁሌም ልምምድ አደርጋለሁ። ያው ወቅቱ አስቸጋሪ ስለሆነ ራሴን ጠብቄ ልምምድ ከሰራሁ በኋላ አብዛኛውን ጊዜየን የማሳልፈው ፊልም በማየት ነው ።

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን ምን እሆናለሁ ብለህ ታስባለህ ?

(እየሳቀ…) እሱን እኔ እንጃ ምናልባት ወደ ትምህርት ነው የማናዘነብለው። ምናልባት በትምህርቱ ነው የምንገፋው እንጂ እንዲህ እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

የማትረሳው ያስቆጠርከው ግብ ? ተቆጥሮባችሁ ያደነቅከው ግብ ?

የማልረሳው እና አሁንም አዕምሮዬ ውስጥ ያለው ከ’ቢ’ አድጌ ደቡብ ፖሊስ ላይ  የስቆጠርኩት የጭንቅላት ግብ ነው። ያኔ ልጅ ነበርኩ። የመጀመሪያ ጨዋታዬ ነበር። በጣም ልዩ ነበር። እነ ጌታነህ ከበደ የነበሩበት ቡድን ነበር ያኔ ደቡብ ፖሊስ። ተቆጥሮብን ያደነቅኩት ግብ ጊዮርጊስ ከጅማ ስንጫወት የጊዮርጊስ ተከላካይ ከርቀት ያስቆጠረብን ግብ በጣም ያምር ነበር።

በተቃራኒ ስትገጥመው ይከብደኛል የምትለው ተጫዋች ?

ሜዳ ውስጥ ስገባ ይከብደኛል ብዬ የማስበው ተጫዋች የለም። ግን ብዙ ጊዜ አብርን ስለተጫወትን ስለሚያውቀኝም ትንሽ አምስሳሉ ጥላሁን (ሳኛ) ።

አንድ ቡድን ውስጥ አብረኸው መጫወት የምትፈልገው ተጫዋች አለ ?

አሁን እግርኳስን አቁሟል ግን አብሬው መጫወት የምፈልገው እና የምመኘው የነበረው ዮርዳኖስ ዓባይን ነበር።

እግርኳስ ውስጥ የቅርብ ጓደኛህ ማነው ?

ብዙ ጓደኞች ነው ያሉኝ አንዱን ከአንዱ መለየት ይከብዳል ግን ብዙ ጊዜ አብሪያቸው የተጫወትኩ ሌላ ክለብ ስሄድም ግንኙነታችን ያልቆመው ያሬድ ዘውድነህ ፣ ቴዎድሮስ ጌትነት ፣ መድሃኔ ታደሰ እና አምሳሉ ጥላሁን ናቸው። ሌሎችም አሉ በሁሉም ክለቦች በሄድኩበት ተግባብቼ ከሁሉም ጋር ጥሩ ግንኙነት ኖሮኝ ነው የምጫወተው።

በእግርኳስ ያዘንክበት እና ደስተኛ የሆንክበት ቀን ?

ጊዜውን አላስታውስም ግን ሱፐር ሊግ ከመድን ጋር ስንጫወት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማለፍ ነበር ጨዋታው ያንን ጨዋታ ስንሸነፍ ነበር በጣም ያዘንኩት። ደስተኛ የሆንኩበት ጨዋታ ደግሞ ጎንደር ላይ መጥተን ፋሲልን አሸንፈን ወደ ፕሪምየር ሊግ የገባንበት ነው። ሁለቱም አጋጣሚዎች ኒያላ እያለሁ ነው ።

እግርኳስ ሜዳ ላይ ያሳቀህ ገጠመኝ ?

አዲስ አበባ ስታድየም ገና ኒያላ እያለሁ ገና ከቢ እንዳደግኩ ነው። እና የኛ ተጫዋች ወደ ግብ የመታውን የሚገባ ኳስ ያዳንኩበት አጋጣሚ አስታውሳለሁ። ቀጥሎ ያኔ የቡና እና የጊዮርጊስ ጨዋታ ነበር። ስታድየሙ ሙሉ ነበር እና ሙሉ ስታዲየም ሰው ነው የሳቀው ፤ ያ አጋጣሚ ያስቀኛል።

ከዚህ በኋላ በእግርኳስ ማሳካት የምትፈልገው ስኬት ?

ከሁሉም ነገር በላይ አሁን ማሳካት የምፈልገው ነገር የፕሪምየር ሊግን ዋንጫ መውሰድን ነው። ያንን ማሳካት እፈልጋለሁ እሱን ማሳካት ከዚህ በኋላ ያለኝ ፍላጎት ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ