​መቐለ 70 እንደርታ እና የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጉዳይ ?

በአፍሪካ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ኢትዮጵያን የሚወክለው መቐለ 70 እንደርታ ከአንድ ሳምንት በኋላ ያለበትን ጨዋታ አሰመልክቶ በምን ሁኔታ ይገኛል?

የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ መቐለ 70 እንደርታ እና የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ ፋሲል ከነማ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ይታወቃል። ከሊቢያው አህሊ ቤንጋዚ ጋር የመጀመርያ ዙር ጨዋታውን የተደለደው ኢትዮጵያዊው ክለብ መቐለ 70 እንደርታ በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ላይ ከህዳር 18-20 ከሜዳው ውጭ የሚጫወት ይሆናል። የመልሱን ጨዋታ ከአንድ ሳምንት በኃላ በሜዳው ከ25-27 ባሉት ቀናት እንደሚያደርግ መርሐግብር መውጣቱ ይታወቃል። ሆኖም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የመቐለ 70 እንደርታን ለጨዋታው ያለው ቅድመ ዝግጅት ምን እንደሚመስል መረጃ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም ቡድኑ ዕለት በዕለት ለካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ልምምዱን እየሰራ እንደሆነና ነገሮች መልክ እየያዙ ከመጡ አልያም አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማመቻቸት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለጨዋታው ጉዞ ለማድረግ እንዳሰቡ ሰምተናል። ከዚህ ውጭ አራት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ዳንኤል አጃይ፣ አዳማ ሲሴኮ፣ ኦኪኪ አፎላቢ እና ካሉሽሀ አል ሀሰን እንዲሁም ሥዩም ተስፋዬ እና አሚን ነስሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መኪና ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን አረጋግጠናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእግርኳሱ የበላይ አካል የሆነው ፌደሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም ሶከር ኢትዮጵያ ባላት መረጃ መሠረት ፌዴሬሽኑ ከመቐለ ክለብ ጋር ምንም አይነት የመረጃ ልውውጥ እያደረገ ባይገኝም ከካፍ አመራሮች እና ከውድድሩ ኤክስፐርቶች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነና የደረሰበትን ሁኔታ በቅርቡ ለሚዲያ እንደሚያሳውቅ ለማወቅ ችለናል።

ከዚህ ጉዳይ አስመልክቶ የሚወጡ መረጃዎች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።

©ሶከር ኢትዮጵያ