​የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል

በታንዛንያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።

በጠንካራ ምድብ ከኬንያ እና ከሱዳን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንዲሁም ምክትሉ ነጻነት እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በለጠ ወዳጆ እየተመራ ያለፉትን 18 ቀናት አንድ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በማድረግ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲሰራ ቆይቷል።

በመጀመርያ ጥሪ ከተደረገላቸው 35 ተጫዋቾች መካከል 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን እያደረገ ባለበት ወቅት ድንገት ስምንት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ ከቡድኑ ውጭ በመሆናቸው የአሰልጣኙን ሥራ ከባድ ቢያደርገውም በምትካቸው ሌሎች ተጫዋቾችን በመያዝ ሲዘጋጅ ቆይቷል።

በነገው ዕለት ወደ ታንዛንያ የሚጓዘው ቡድኑ በትናንትናው ዕለት የኮቪድ ምርመራ ያደረገ ሲሆን በቡድኑ ውስጥ ከተያዙት 21 ተጫዋቾች መካከል አንድ ግብጠባቂን በመቀነስ 20 ተጫዋቾችን በመያዝ የሚጓዝ ይሆናል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና ረዳቶቹ

ዛሬ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ያደረገው ወጣት ቡድኑ እጅግ የተደራጀ እና የተሟላ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተመልክተናል። ቡድኑ በሁሉም ረገድ በተለይ በሴካፋ ዋንጫ ከዚህ ቀደም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የያዘ መሆኑና እንዳላቸው አቅም ጥሩ ውጤት ይዘው ይመለሳሉ ተብሎ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

ቡድኑ ሰኞ ኅዳር 14 ቀን 2013 የምድቡ የመጀመርያ ጨዋታውን ከኬንያ ጋር በማድረግ ከሁለት ቀን በኋላ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታውን ረብዕ ኅዳር 16 ቀን ከሱዳን ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ