አስራት መገርሳ ሌላው የወልዋሎ ፈራሚ ሆኗል

ከሊጉ ለመሰናበት ከጫፍ ደርሰው ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወልዋሎ ዓ.ዩ በቁጥር የበረከቱ ተጨዋቾችን በማስፈረም እየመራ ይገኛል። በተለይም ዛሬ እየወጡ ያሉት አብዛኛዎቹ የዝውውር ዜናዎች ከሰሜኑ ክለብ ጋር የሚገናኙ ሆነዋል። ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ከቻለው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ አንዱ የነበረው አስራት መገርሳም የክለቡ ሌላኛው አዲስ ተጨዋች መሆኑ ተረጋግጧል።

ቁመተ መለሎው አማካይ ያደገበትን ኢትዮ ኤሌክትሪክን በአምበልነት እስከመምራት በመድረስ ለቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ሆኖ ካሳለፈ በኋላ ወደ ዳሽን ቢራ አምርቶ ነበር። የዳሽን ቢራን መበተን ተከትሎ ደግሞ ያለፉትን ሁለት የውድድር አመታት ከደደቢት ጋር መቆየት ችሏል። ደደቢት በፋይናንስ ችግር ምክንያት ትልቅ ስም ያላቸውን ተጨዋቾቹን እየለቀቀ ባለበት ሰዐት ደግሞ አስራት የቡድን ጓደኖቹ የነበሩት ክሌመንት አዞንቶ ፣ ብርሀኑ ቦጋለ፣ ደስታ ደሙ እና ኤፍሬም አሻሞን ተከትሎ ወደ ቢጫ ለባሾቹ ቤት ሄዷል።

የቡድኑን የተከላካይ አማካይነት ሚና በአሳሪ አልመሀዲ እና ብርሀኑ አሻሞ ይሸፍኑ የነበሩት ወልዋሎዎች አሳሪ በመከላከያው ጨዋታ ላይ በዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴ ድብደባ ምክንያት ለቅጣት በመዳረጉ ቦታውን ለመሸፈን አማራጫቸው ጠቦ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ይመስላል አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በቦታው የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው አስራት መገርሳን ወደ ክለቡ እንዲመጣ አድርገዋል።