ሞገስ ታደሰ ሁሉም ከጎኑ እንዲቆም ይጠይቃል

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ሞገስ ታደሰ ከገጠመው ህመም ይድን ዘንድ ሁሉም እንዲረዳው ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ከአዲሱ ሚሌኒየም ወዲህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ካሉ ተጫዋቾች መካከል ሞገስ ታደሰ አንዱ ነው። በክለብ ደረጃ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግርኳስ ክለብ ወጠች ቡድን ጅማሮውን ያደረገው ተከላካዩ በሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት የተጫወተ ሲሆን በተለይም በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ውጤታማው ቡድን ውስጥ መካተት ችሎ ነበር።

ሆኖም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጨረሻ  በገጠመው ህመም ይህ ተጫዋች ዛሬ ላይ በቤቱ ይገኛል፡፡ በአዳማ የባጃጅ አደጋን በማስተናገድ በግራ እጁ ላይ የቀዶ ጥገናን ያደረገው ሞገስ ከአደጋው በኋላ በኤሌክትሪክ ከቆየ በኋላ አምና ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ወደ ወልዲያ ቢያመራም ከህመሙ ጋር እየታገለ ለመጫወት ሲሞክር ቆይቷል። ነገር ግን ህመሙ እየተባባሰ ሄዶ ላለፉት አስር ወራት ያህል በእጆቹ እና እግሮቹ ላይ በፈጠረበት ዕክል ከሜዳ ለመራቅ ተገዷል፡፡ የነርቭ ሞተሩ በመጎዳቱም አሁን ላይ ከቤቱ መውጣት  ያቃተው ተከላካዩ በእጁ ላይ ጅማሮን ያደረገው በሽታው እንደልብ እንዳይንቀሳቀስ አስገድዶት ይገኛል፡፡

የሞገስ ታደሰን የህክምና ሂደት ለመከታተል እና ድጋፉንም ለማስተባበር ኮሚቴ እየተቋቋመ ሲሆን ኮሚቴው ስራውን እስከሚጀምርም በወላጅ እናቱ ወ/ሮ ሠርክዓለም አለባቸው ቦጋለ ስም የሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ለበጎ ፈቃደኞች ተዘጋጅቷል። በጎ አድራጊዎችም ገንዘቡን ሲያስገቡ የተመዘገበበትን ስም እንዲያረጋግጡ እና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።

ስም ፡ ወ/ሮ ሠርክዓለም አለባቸው ቦጋለ

የሂሳብ ቁጥር ፡
 1000247375418


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *