ፀጋዬ አበራ ለየት ስላለው ደስታ አገላለፁ ይናገራል

የአርባምንጭ ከተማው የመስመር አጥቂ ትናንት ቡድኑ አዲስ አበባ ከተማን 2-1 ሲረታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ስላሳየው የደስታ አገላለፅ አብራርቷል።

እግር ኳስን በአርባምንጭ ከተማ በተከላካይ መስመር ቦታ ላይ በመጫወት የጀመረው ፀጋዬ አበራ ወላይታ ድቻን ሲቀላቀል በፊት አጥቂነት እንዲሁም ደግሞ በመስመር አጥቂነት ስፍራ ላይ ሆኖ በመጫወት አሳልፏል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሽ ከወላይታ ድቻ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደ ልጅነት ቡድኑ አርባምንጭ በመመለስ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ከፍ እንዲል ድርሻው ላቅ ያለ ነበር።

በአርባምንጭ የዘንድሮው የሊጉ ተሳትፎ ውስጥም ቡድኑ በቀላሉ ግብ የማያስተናግድ አወቃቀር እንዲኖረው ካደረጉ እና ከመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከማይጠፉ ተጫዋቾች ውስጥ ይካተታል። በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ታምኖበት በመስመር ተጫዋችነት እያገለገለ የሚገኘው ፀጋዬ እንደ ቡድን ጓደኞቹ ሁሉ በትጋት በመንቀሳቀስ ይታወቃል። ‘ተጋጣሚ ላይ ከፍ ያለ ጫና በማሳደር መጫወት የእኛ መለያ ቀለም ነው’ የሚለው ተጫዋቹ ይህንን አጨዋወት ከማስፈፀም አንፃር ለአዞዎቹ ያለውን እየሰጠ ቢቆይም በግብ አስቆጣሪዎች መዝገብ ውስጥ ሳይሰፍር ቆይቶ ነበር።

ትናንት ምሽት በተደረገው እና አርባምንጭ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 2-1 በረታበት ጨዋታ ግን ፀጋዬ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ በማገናኘት ቡድኑን ሦስት ነጥብ ያስጨበጠበትን ድንቅ ቀን አሳልፏል። ተጫዋቹ ሁለተኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ጥቁር ፌስታል በመልበስ ደስታውን የገለፀበት መንገድ ግን ትኩረት የሳበ ነበርና ምክንያቱን ተጠይቆ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ሲል ተናግሯል።

“ጎል በማስቆጠሬ በጣም ደስ ነው ያለኝ ፤ በዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት ጎሎችን ነው ያስቆጠርኩት ለእኔ ልዩ እና የተለየ ቀን ነበር፡፡ ሁለተኛው ጎል ካስቆጠርኩኝ በኋላ የተለየ ነገርን ለተመልካቹ ለማሳየት ፈልጌ ነበር፡፡ያሳየሁት የደስታ አገላለፅ በሳውዲ ያሉ ወገኖቻችን ለማሰብ ብዬ ያደረኩት ነው። “