ሻሸመኔ ከተማ ቀጣይ ጨዋታውን በጊዜያዊ አሰልጣኝ ይመራል

የአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን መልቀቂያ በይፋ የተቀበለው ሻሸመኔ ከተማ በቀጣይ በጊዜያዊ አሰልጣኝ ይመራል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ረዘም ካሉ ዓመታቶች በኋላ ብቅ በማለት በዘንድሮው የሊጉ ጉዞ እየተካፈለ የሚገኘው ሻሸመኔ ከተማ ከታችኛው የሊግ ዕርከን ባሳደገው አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ እየተመራ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ያደረገ ሲሆን አሰልጣኙ ከሲዳማ ቡናው ሽንፈት በኋላ ባሉት ቀናት በክለቡ ውስጥ መቀጠል ባለመፈለጋቸው መልቀቃቸውን ከቀናት በፊት በዘገባችን ጠቁመናችሁ ነበር።

አሰልጣኝ ፀጋዬም በትላንትው ዕለት በይፋ ለክለቡ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው ክለቡን መሰናበታቸው የታወቀ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ አንድም ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑም በቀጣይ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታውን የፊታችን ማክሰኞ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ሲያደርግ በምክትል አሰልጣኝነት ክለቡን ሲያገለግል የነበረው በቀለ ቡሎ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ክለቡን እንደሚመራው ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ ከዚህ ቀደም የሻሸመኔ ከተማ የሴት ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመራ ሲሆን ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደግሞ የወንድ ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል። በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻው ግርጌ ላይ ያለምንም ነጥብ በ5 የግብ ዕዳ የተቀመጠው ክለቡ በቅርብ ቀናትም አዲስ ዋና አሰልጣኝ እንደሚሾም ይጠበቃል።