በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደቡብ ደርቢ ይርጋለም ላይ የተገናኙት ሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታቸውን ያለግብ አጠናቀዋል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የተከታተሉት ይህ ጨዋታ ሲዳማ ቡና የደበዘዘው የዋንጫ ተስፋን ለማለም እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ካለበት የመውረድ ስጋት ከመላቀቅ አንፃር ብርቱ ትግል ያደረጉበት ነበር። በጨዋታውም እንዳለ ከበደ ፣ ተመስገን ካስትሮ እና ገብረሚካኤል ያዕቆብ በአርባምንጭ በኩል አንተነህ ተስፋዬ ፣ አበበ ጥላሁን እና ሙሉአለም መስፍን ደግሞ በሲዳማ በኩል የቀድሞ ክለባቸውን የገጠሙ ሲሆን የአርባምንጭ ከተማዎቹ ታደለ መንገሻ እና ተሾመ ታደሰ በጉዳት ጨዋታው አምልጧቸዋል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እና በዘነበው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው እንቅስቃሴ ለማድረግ አስቸጋሪ የሆነበት እንዲሁም አምስት የቢጫ ካርዶችን ጨምሮ በርካታ ጥፋቶች እና ሽኩቻወች የታዩበት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች አዞወቹ ፈጣን የማጥቃት ባህሪን በባለሜዳው ሲዳማ ቡና ላይ አሳይተዋል። በዕለቱ ድንቅ የነበረው ወንድሜነህ ዘሪሁን ከገብረሚካኤል ጋር አንድ ሁለት ቅብብል በማድረግ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ገብተው ገብረሚካኤል የሞከረውን እንዲሁም 9ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ ያሻገረውንን ቅጣት ምት በመጠቀም ተመስገን ካስትሮ በግንባሩ የገጨውን እና አሁንም በድጋሜ ወንድሜነህ ከማእዘን ምት ያሻማውን ተመስገን ካስትሮ በግንባር የሞከረውን ኳሶች ለአለም ብርሀኑ አደነባቸው እንጂ አርባምንጮች ቀዳሚ መሆን በቻሉ ነበር ።
ከዚህም በኋላ ሲዳማ ቡና ወደ ጨዋታው ሪትም በፍጥነት በመመለስ በማጥቃት ተጫውቷል። የሲዳማ ቡና የመሀል ሜዳ ተጫዋች የሆነው ፍፁም ተፈሪ የሚያሻግራቸው ረጃጅም ኳሶች ለፈጣኑ አጥቂ አዲስ ግደይ በተደጋጋሚ ቢደርሱም ሜዳው ውሀ በመቋጠሩ ምክንያት ጥረታቸው ሲከሽፍም ታይቷል። በዚህ የጨዋታው መጀመሪያ 45 ደቂቃዎችም በተደጋጋሚ ተጨዋቾች በሜዳ ላይ እርስ በእርሳቸው በሚፈጥሩት ግጭት ሳቢያ ኢንተርናሽናል ዳኛ ዘካሪያስ ግርማ 5 ቢጫ ካርዶችን መዘዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች የበላይ የሆኑበት እና አርባ ምንጮች ደግሞ አልፎ አልፎ የግብ ዕድል የፈጠሩበት ነበር ። በጨወታው ሲዳማዎች ሙሉአለም መስፍንን ቀይረው ማስገባታቸው የመሀል ሜዳውን ለማረጋጋት እጅጉን ጠቅሟቸው ታይቷል ። በ63ተኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከግራ መስመር የመታት ቅጣት ምት ማንም ሳይደርስባት የቀኝ ቋሚውን ነክታ የወጣችበት እና በመልሶ ማጥቃት ከተገኘ ኳስ ሰንደይ ሙቱክ ከመስመር አሻምቶት ላኪ ሰኒ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት ኳስ የሲዳማዎች ጥሩ ሙከራዎች ነበሩ ። በ76 ተኛው ደቂቃ ላይም ፀጋዬ ባልቻ ያሻማትን የማዕዘን ምት ሰንደይ በግንባሩ ሲገጭ እና ሲመለስበት ሙሉአለም ሞክሮ የአርባምንጭ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡበት አጋጣሚም ቡድኑን ለጎል ያቀረበች ነበረች ። ከዚህ ውጪ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቀይሮ የገባው ኤሪክ ሙራንዳ አክርሮ የመታት ኳስም የግቡን ቋሚ ለትማ ወደ ውጭ ወጣች እንጂ የሲዳማን አሸናፊነት ማረጋገጥ ምትችል ሙከራ ነበረች ። በአዞወቹ በኩል ወንድሜነህ ዘሪሁን በተደጋጋሚ ከሚመታቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራወች ሌላ ምንተስኖት አበራ ከቅጣት ምት አክርሮ የመታት እና ለአለም በቀላሉ የያዘበት ኳስ የሚጠቀሱ የቡድኑ ሙከራዎች ነበሩ።
በርካታ ደጋፊዎች በሁለቱም ክለቦች በኩል በልዩ ሁኔታ ይሰጡት በነበረው ድጋፍ እና በዝናቡ በመታጀብ ማራኪ እንቅስቃሴ እየታየበት የቀጠለው የቡድኖቹ ፍልሚያ በመጨረሻም በቀይ ካርዶች ነበር የተጠናቀቀው ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ያለወትሮ በተከላካይ ቦታ ላይ ተሰልፎ የተጫወተው የአርባምንጭ ከተማው ፀጋዬ አበራ ከ ኤሪክ ሙራንዳ ጋር በፈጠረው ግጭት በአልቢትር ዘካሪያስ ግርማ የቀይ ካርድ ሰለባ ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀር ደግሞ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱክ በአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ ፂሆን መርዕድ ላይ አደገኛ አጨዋወት በመጫወቱ በተመሳሳይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል ። በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ የታዩትን ስድስት የቢጫ ካርዶች ጨምሮ በጨዋታው በአጠቃላይ አስራ አንድ ቢጫ ካርዶች እና ሁለት ቀይ ካርዶች ታይተዋል ። ቀዝቃዛ እና ዝናባማ የአየር ሁኔታ ከጠንካራ የደርቢ ስሜት ጋር ያስተናገደው ጨዋታም የሲዳማ ቡናን የማጥቃት እንዲሁም የአርባምንጭ ከተማን ጠንካራ የመከላከል አጨዋወት አስመልክቶን በዚህ መልኩ ያለምንም ግብ ተጠናቋል፡፡