በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር እጅግ ወሳኝ የተባለው የወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አአ ከተማን ተከትለው የሚወርዱ ሁለት ክለቦችን የመለየት ሒደቱም አጓጊ መልክ እንዲይዝ አድርጓል፡፡
በጨዋታው ወላይታ ድቻ አአ ከተማን ከገጠመው ቡድኑ ዮሴፍ ደንገቶን አሳርፎ አላዛር ፋሲካን በማስገባት ለውጥ አድርጎ ሲጀምር ንግድ ባንክ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናን ከገጠመው የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ሮቤል ግርማን በአቤል አበበ ፣ ዮናስ ገረመውን በታዲዮስ ወልዴ ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ በዋና ዳኝነት በመሩት ጨዋታ ቁጭ ብድግ የሚያደርግ እና ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር የታየበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ብቻ ፈልገው ወደ ሜዳ የገቡ እንደነበር የሚያሳይ ነፃ የኳስ ፍሰት በበርካታ የጎል ሙከራዎች ታጅቦ ተካሂዷል፡፡
በመጀመርያው አንድ ደቂቃ ላይ እንግዶቹ ንግድ ባንኮች ቢኒያም አሰፋና ቢንያም በላይ የድቻ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ በአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ገብተው ቢኒያም አሰፋ ያመከነው የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። በዚህ ደቂቃ ውስጥ በፍጥነት ወደ መልሶ ማጥቃት የተሻገሩት ድቻዎች ፀጋዬ ብርሃኑ በቀኝ መስመር አፈትልኮ በመግባት ጣጣውን ጨርሶ የሰጠውን ኳስ ዳግም በቀለ አገባ ሲባል የሳተው ኳስ ለድቻዎች የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታው በአስገራሚ ግለት ቀጥሎ 4ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻ በቀኝ መስመር ተከላካይና አጥቂ የነበሩት ፈቱዲን ጀማል እና ፀጋዬ ብርሃኑ በጥሩ የመስመር ጨዋታ በመግባት በተመሳሳይ ፀጋዬ ብርሃኑ ያሻማውን ዳግም በቀለ በድጋሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ሜዳው ላይ በጣለው ዝናብ ምክንያት ለሁለቱም ቡድኖች ኳስን መስርቶ እና አሸራሽሮ ለማጫወት አዳጋች በመሆኑ ያሰቡትን ታክቲክ ለመተግበር የቸገራቸው ሲመስል በተመሳሳይ አጨዋወት ሁለቱም ቡድኖች በረጃምም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም በዚህ አጨዋወት ወላይታ ድቻ ተጠቃሚ ሲሆን ታይቷል። በተለይ ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ጎል በሚጣሉ ኳሶች አላዛር ፋሲካ እና ዳግም በቀለ ይፈጥራቸው የነበሩ የጎል እድሎች ለንግድ ባንክ ተከላካዮች እና ለአማኑኤል ፌቮ ፈታኝ ነበሩ። በአንፃሩ የንግድ ባንክ ተጨዋቾች በረጅሙ የሚጥሉት ኳሶች መድረሻ ሳይኖራቸው ይባክኑ ነበር። ያም ቢሆን ንግድ ባንክ አልፎ አልፎ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ቢኒያም አሰፋ 19ኛው ደቂቃ ላይ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምት የቀረው ኳስ ለንግድ ባንክ የሚያስቆጭ ነበር። ጨዋታውም በመጀመርያው 30 ደቂቃ ውስጥ በነበረው ፍጥነት ሳይቀጥል ቀዝቀዝ እያለ አስደንጋጭ የጎል ሙከራ ሳይደረግበት ጥንቃቄ ተሞላበት አጨዋወት የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ ወላይታ ድቻ ተዳክመው ፣ ንግድ ባንክ ተሽለው የቀረቡበት ሆኖ ታይቷል፡፡ በርካታ ውዝግቦች እና የደጋፊ ነውጥ ፣ ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ እና ወሳኝ ግብ የተስተናገደበት ሆኗል፡፡
በሁለቱም በኩል የተለየ የአቀራረብ ለውጥ ይዘው ያልገቡ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ሲያደርጉ እነደነበረው በረጃጅም ኳሶች እና ከቆሙ ኳሶች ጎልን ለማስቆጠር ይጥሩ ነበር። በ50ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ቢንያም ሲራጅ በግንባሩ ከመሬት ጋር አጋጭቶ ሞክሮ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣበት ሙከራ ከእረፍት መልስ የመጀመርያው ነበር። ጨዋታው ኃይል የተቀላቀለበት ሆኖ እየቀጠለ ባለበት ሰአት 56ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ አላዛር ፋሲካ ላይ አላስፈላጊ ሀይል ተጠቅመሀል በማለት ታዲዮስ ወልዴን በሁለት ቢጫ ከሜዳ አስወግደውታል፡፡ ግርማ በቀለ በክርኑ ተመትቶ በዝምታ አልፍሀል በሚል በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት የንግድ ባንክ ተጨዋቾች እና የቡድኑ አባለት ወደ ሜዳ በመግባት ቅሬታ ሲያቀርቡ በነበረው ውዝግብ እና ክርክር ጨዋታው ለአምስት ደቂቃ ያህል ሊቋረጥ ችሏል።
ከተቋረጠበት የቀጠለው ጨዋታ ሲቀጥል አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ በመሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው በፍጥነት የአጥቂ ክፋላቸውን ቁጥር በመቀነስና ቢንያም አሰፋን በዮናስ ገረመው በመተካት የመሀል ሜዳ ክፍሉን ማመጣጠን ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በአንፃሩ የአንድ ተጨዋች መቀነስን በመጠቀም የተከላካይ ቁጥራቸውን በመቀነስ የአጥቂ ቁጥራቸውን ያበዛሉ ቢባልም ከ15 ደቂቃ መዘግየት በኋላ የተመሳሳይ ሚና ለውጦች በማድረግ ተመስገን ዱባን በዳግም በቀለ እንዳለ መለዮን በፀጋዬ ብርሃኑ ቀይረዋል።
ታዲዮስ ወልዴ በቀይ ካርድ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የረባ እንቅስቃሴ ያልተመለከትንበት ጨዋታ ሲሆን በተደጋጋሚ በሁለቱም ቡድኖች በሚፈፀሙ ሀይል የተቀላቀለበት አጨዋወት የተነሳ ጨዋታው በዳኛው ፊሽካ ይቆራረጥ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች አልፎ አልፎ ከሚያደርጉት ያልተሳካ የኳስ ቁጥጥር ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ የጎል ሙከራም አልነበረም። ሆኖም ግን በቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ንግድ ባንኮች 80ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው የግል ብቃቱን ተጠቅሞ አምስት ከሃምሳ ውስጥ አመቻችቶ ያቀበለውን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ያመከነው ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
ጨዋታውም በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ይችላል በተባለበት አጋጣሚ 90ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ከቀኝ መስመር ሰብሮ ወደ ድቻ የግብ ክልል በመግባት መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ወርቃማ የሆነ ግሩም ጎል አስቆጥሯል ። የጎሉን መቆጠር ተከትሎ የንግድ ባንክ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ አስገራሚ ሲሆን በአንፃሩ በስቴዲዮሙ የተገኙት ደጋፊዎች በሙሉ በጎሉ መቆጠር መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ የተጨመረው አራት ደቂቃ ማብቂያ ላይ ፒተር ኑዋዲኬ ሜዳው ላይ ጥፋት ተሰርቶብኛል በማለት መውደቁን ተከትሎ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ቁጣቸውን የገፁ ሲሆን የተለያዩ ቁሳቁሶች እና ድንጋይ ወደ ሜዳው በመወርወራቸው ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጧል። ከደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ ብዙም ሳይቆይ የዕለቱ ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቂያ ፊሽካ አሰምተው ጨዋታው በንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በመጨረሻም ውጤቱን በፀጋ መቀበል የተሳናቸው የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው ቁሳቁስ በመወርወር የፈጠሩት ረብሻ በፍፁም መደገም የሌለበት ተግባር መሆኑን እየገለፅን የእግር ኳስ አካል የሆነውን መሸነፍን በፀጋ የመቀበል ባህል እንዲያዳብሩ መልክታችንን እናስተላልፋለን፡፡