የከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙርን በተመለከተ ውይይት ተደረገ

ከተገባደደ ከሁለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረው የመጀመርያው ዙር የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ከአወዳዳሪ ኮሚቴው ጋር ውይይት አድርጓል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የከፍተኛ ሊግ ዋና ሰብሳቢ አቶ አሊሚራ መሐመድ፣ ዋና ፀሐፊው አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የዳኞች ዋና ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም አህመድ እንዲሁም የክፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በኢሊሊ ሆቴል ውይይት አከናውነዋል።

በስብሰባ የሁለተኛ ዙር ውድድር ከዚህ ቀደም እንዲካሄድ በታቀደባቸው ከተማዎች ማለትም በሀዋሳ፣ ወልዲያ እና ነቀምቴ እንዲቀጥሉ ውሳኔ ሲያሳልፍ የሁለተኛ ዙር ውድድር እንዲካሄድባቸው በፌደሬሽኑ ተጠቁመው የነበሩት ሦስቱ ከተሞች ጉዳይ በተለያዩ ክለቦች በርካታ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቢቆይም በፌዴሬሽኑ የዛሬ ስብስባ ቅሬታዎቹን ውድቅ በማድረግ በተቀመጠላቸው ከተማ ለማካሄድ ወስኗል።

በመጀመሪያው ዙር ውድድር ከፍተኛ ወቀሳ ሲቀርብበት የነበረው የዳኝነት ጉዳይ በጥልቀት የተነሳ ሲሆን በክለቦች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን የፈጠረው የዳኝነት ችግር መኖራቸውን ያመነው ፌዴሬሽኑ በሁለተኛው ዙር እነዚህን ስህተቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማሻሻል እንደሚሰራ ገልጿል።

በቀጣይ ቡድኖች ከየኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር ውይይት የሚደርጉ ሲሆን ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ያላጠናቀቁ ቡድኖች ክፍያ እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል። እንዲሁም ቅጣት የተጠላባቸው ተጨዋችም ሆነ ቡድኖች ክፍያቸውን ካላጠናቀቁ በሁለተኛው ዙር ውድድር ላይ እንደማይሳተፉ ተገልጿል።

የሁለተኛ ዙር ውድድር በመጋቢት 13 በሃዋሳ፣ በወልዲያ እና በነቀምቴ ከተሞች የሚጀምር ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ