በዝውውር ገበያው ላይ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ከደቂቃዎች በፊት ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።
አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከቀናት በፊት የሾመው ሰበታ ከተማ ወዲያው ወደ ዝውውሩ በመግባት ተጫዋቾችን እያደነ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሃኑ እና አማካዩ አዲስዓለም ደበበ ቡድኑን መቀላቀላቸውን ያመላክታል።
የቀድሞ የደቡብ ፖሊስ፣ መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ተጫዋች የነበረው ለዓለም 2010 ላይ ወደ መዲናው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመምጣት ግልጋሎት መስጠቱ ይታወቃል። ከለዓለም በተጨማሪ የቀድሞ የሲዳማ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ተጫዋች የነበረውና ያለፈውን የውድድር ዘመን በሻሸመኔ ከተማ የነበረው አዲስዓለም ደበበ ቡድኑን ተቀላቅሏል። ሁለቱም ተጫዋቾች በሰበታ ለሁለት ዓመት ግልጋሎት ለመስጠት መፈረማቸው ታውቋል።