በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ከአሰልጣኞች ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ተመልክተናል።
👉 እኔ ፣ እኔ ፣ እኔ…
በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ የቡድን ሥራ መንፈስ እምብዛም የተለመደ አይደለም። በአብዛኛው መስኮች ላይ የራስን ሥራ አግዝፎ ለመሳየት የሚደረጉ ጥረቶችን በስፋት እናስተውላለን። በተለይ ደግሞ ይህ አስተሳሰብ በኃላፊነት ላይ በሚገኙ አሰልጣኞች ላይ በስፋት ይንፀባረቃል።
ይህ እሳቤ በተለይ ቡድኖች በውጤታማነት ጉዞ ላይ በሚገኙበት ጊዜ አሰልጣኞች በሚዲያ በሚቀርቡባቸው ወቅቶች ሁሉ ከቡድኑ ስኬት በስተጀርባ ያለውን እውቅና ለራሳቸው የመጠቅለል ዝንባሌን የምናስተውል ሲሆን በተቃራኒው ውጤት ሲጠፋ እና ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ ወደ ሌሎች ጣት የመቀሰር እና ኃላፊነትን የማሸሽ ዝንባሌ በእግርኳሳችን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ አሰልጣኞች የጋራ መገለጫ ባህሪ ነው።
በሀገራችን አውድ ሜዳ ላይ የአሰልጣኙን ሀሳብ ለመተግበር ከሚታትሩት ተጫዋቾች ባለፈ ጥቂት የአሰልጣኝ ቡድኖች አባላት ሆነ ሌሎች የቡድኑን ሥራ የሚያግዙ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች እንዳሉ ይታወቃል። ታድያ የዋና አሰልጣኙ ሥራ እነዚህን አካላት በማስተባበር ከበላይ ሆኖ የውሳኔ ሰጪነት ሚና መስጠት እንደሆነ ይታመናል። ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ ዋና አሰልጣኞች ከታች የቡድኑ ትጥቅ ያዥ አንስቶ እስከ ላይኛው ምክትል አሰልጣኞች ድረስ ለቡድኑ ለሚሰጡት አበርክቶ እውቅና መስጠት ግዴታ ባይሆንም ጥሩ የጋራ ስሜትን ከመፍጠር አንፃር ይጠበቅባቸዋል።
ከምልመላ እስከ የጨዋታ ዕቅድ ከተጫዋች ቅያሬ እስከ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ድረስ ዋና አሰልጣኞች በሚዲያ ፊት ቀርበው “በድል ሽሚያ” እሳቤ ያደረኩት ፣ የቀየርኩት ፣ ያመጣሁት እና ሌሎችም “የእኔ ብቻ” እሳቤ የተጠናወታቸውን ንግግሮች ሲያደርጉ በተደጋጋሚ አስተውለናል።
እርግጥ በሀገራችን ካለው ደካማ እግርኳሳዊ መዋቅር አንፃር ዋና አሰልጣኙ በርካታ ሚናዎችን ሊወጣ ይችላል ብለን እንኳን ብናስብ በአጠገቡ ለሚገኙ ባለሙያዎች ክብር ሲባል እኛ የሚል የቡድን መንፈስ በውስጣቸው ያዘሉ አባባሎችን ቢጠቀሙ ይመከራል።
እርግጥ በተደጋጋሚ መሰል ንግግሮችን ማድመጥ በተለመደበት አሰልጣኞቹ ባለማወቅ ነው በዚህ መልኩ የሚናገሩት ብሎ ለመውሰድ ቢያስቸግርም አንዳንድ ደግሞ ከዚህ እሳቤ የሚመሩ አሰልጣኞች መኖራቸው ግን መዘንጋት የለበትም። በመሆኑም አሰልጣኞች ከእኔ እሳቤ ወጥተው እኛነትን የሚሰብኩ ንግግሮችን ከእነሱ ብናደምጥ የተሻለ ይሆናል።
👉 “ተጋጣሚን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት አድርገናል”
ለጨዋታዎች የሚደረጉ ዝግጅቶች በመሰረታዊነት የራስን ቡድን ታሳቢ ባደረጉ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነጠ ቢሆንም ቀላል የማይባል ግምት በሚሰጠው መልኩ ደግሞ የተጋጣሚን ሁኔታ ከግምት ያስገቡ ዝግጅቶች መደረጋቸው አይቀሬ ነው።
ታድያ ይህ በሆነበት ሁኔታ አሰልጣኞቻችን በሚሰጧቸው አስተያየቶች በተድበሰበሰ መልኩ “የተለየ ዝግጅት አላደረግንም” በሚል ሀረግ መሰል ጥያቄዎችን ሲያልፏቸው ይስተዋላል ፤ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ምንም እንኳን በጨዋታው ውጤታማ መሆን ባይችሉም የድሬዳዋ ከተማው ዋና አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ተጋጣሚያቸው የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ጥንካሬ በማጥናት ይህን ለማክሸፍ የሚረዳ የጨዋታ ዕቅድ ስለማዘጋጀታቸው ሲናገሩ ተደምጧል።
ይህም በእግርኳሳችን ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት ከሳቡ አስተያየቶች አንዱ ነበር። ከመጋረጃ በስተጀርባ በመጠኑ ይብዛም ይነስም ዝግጅቶችን የሚያደርጉት አሰልጣኞች በአደባባይ የተለየ ዝግጅት ማድረጋቸውን መደበቅ የተለመደ ሲሆን መሰል እውነታን ያዘሉ አስተያየቶች መደመጣቸው የሚበረታታ ነው።
አብዛኞቹ አሰልጣኞች የተለየ ዝግጅት አድርገናል ብለው በአደባባይ ሀሳብ ቢሰጡ እና ነገርግን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ያዘጋጁት የጨዋታ ዕቅድ ውጤታማ ባይሆን የሚፈጠረውን ጫና በመሸሽ እንዲህ ዓይነት አስተያየቶችን ሊሰጡ እንደሚችሉም ይገመታል።
👉 የመልሶ ማጥቃቶች ጉዳይ
አብዛኞቹ የሊጉ ቡድኖች በጨዋታ የበላይነት ወስደው በራሳቸው መንገድ ጨዋታቸውን ከመቃኘት ይልቅ በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ፍላጎት እንዳላቸው እናስተውላለናል። ነገርግን ይህ ነገር በብዛት ከፍላጎት ባለፈ ሜዳ ላይ በሚታይ መልኩ ስል የመልሶ ማጥቃት ቡድኖችን እያየን አንገኝም።
ቡድኖች በዚህ ረገድ ውጤታማ ስላለመሆናቸው ስናነሳ በርካታ ጉዳዮችን በምክንያትነት ማቅረብ ብንችልም ብዙም ልብ ያልተባለው ጉዳይ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚደረጉ የኳስ ቅብብሎች የጥራት ደረጃ ዝቅ ያለ መሆኑ ጉልህ ድርሻን እንደሚወስድ እየተመለከትን እንገኛለን።
የመልሶ ማጥቃት ጨዋታ መሰረታዊው እሳቤ ተጋጣሚ በማጥቃት ጨዋታ ውስጥ ሲሆን ተጫዋቾቹ ከሚኖራቸው የተዘረዘረ ቦታ አያያዝ እና ክፍት ትተዋቸው የሚመጡትን የሜዳ ክፍሎችን ኳሱን ባጡበት ቅፅበት ሳይደራጁ መጠቀም እንደሆነ ይታወቃል። ታድያ በዚህ ሂደት ውስጥ መልሶ ማጥቃቱን የሚሰነዝረው ቡድን እጅግ ፈጣን መሆን ካልቻለ ጥረቶቹ ሁሉ መና መቅረታቸው አይቀርም።
ስለፍጥነት ስናስብ መነሻ የሚሆነን ነገር ኳስ ተጋጣሚ ከተነጠቀበት የሜዳ ክፍል እስከ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለማድረስ የሚወስደው ጊዜ በጣም አጭር መሆን ይገባዋል በዚህም የተጫዋች አማራጮች እስካሉ ድረስ ፈጣን እና ቀጥተኛ የኳስ ማቀበል ሂደቶች በጣም ወሳኝ ናቸው።
እነዚህ ቀጥተኛ እና ወደ ፊት የሚደረጉ ቅብብሎች ግን በተጠና መልኩ የቡድን አጋሮችን እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ እና ከፊታቸው የሚገኙ ክፍት ሜዳዎች ላይ መዳረሻቸውን ያደረጉ መሆን ይገባቸዋል። ይህ ሂደት ግን በሀገራችን ብዙ ሲተገበር አይስዋልም። አብዛኞቹ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ውጤታማ ካለመሆናቸው በስተጀርባ መልሶ ማጥቃት የሚሰነዝረው ቡድን ተጫዋቾች እንቅስቃሴውን በማስቀጠል ሂደት የሚያደረጓቸው ቅብብሎች ተጫዋቾች በተነሱበት ፍጥነት (ፍጥነታቸውን ጨምረው) የሚደርሱባቸው ኳሶች ሳይሆኑ ከተጫዋቾቹ ፍጥነት አንፃር ዝግ ያሉ በመሆናቸው ተጫዋቾች ፍጥነታቸውን ለመቀነስ እና ኳሶቹን በሚፈለገው ፍሰት ውስጥ ከማግኘት ሲያግዳቸው እና ተጋጣሚ በዚህ አጋጣሚ መልሶ የሚደራጅበት ዕድል ሲኖረው ይስተዋላል።
በመሆኑም ይህን አጨዋወት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተጫዋቾቹን ሳይሆን ከተጫዋቾቹ ፊት ያለውን የሜዳ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ ኳሶችን ማቀበል እጅግ ወሳኝ ነው። በዚህ ሂደት በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፋሲል ከነማን በረቱበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ጨዋታዎች የነበራቸው አፈፃፀም ለክለቦች በማስተማርያነት መዋል የሚችሉ ናቸው።
👉 ኃይሉ ነጋሽ የመጀመሪያ ጨዋታውን መርቷል
ከቀናት በፊት ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር የተለያዩት ፋሲል ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በኃይሉ ነጋሽ እየተመሩ ጨዋታቸውን ማድረግ ችለዋል።
በጎንደር እና አካባቢዋ በርካታ ታዳጊ ተጫዋቾችን በማፍራት የተከበረ ስም ያለው ኃይሉ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በፋሲል ከነማ ውስጥ በምክትል አሰልጣኝነት ሲያገለግል ቆይቷል። አሁን ደግሞ የውድድር ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተረከበውን የቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሥራን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጀምሯል።
ለኃይሉ የመጀመሪያው በነበረው ጨዋታ ፋሲል ከነማ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ባስቆጠራት ግብ ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 በመርታት ጣፋጭ ድልን አሳክቷል። በቀድሞ የቡድኑ አምበል ሙሉቀን አቡሀይ ረዳትነት ኃላፊነቱን የተረከቡት ሁለቱ አሰልጣኞች ነገሮችን ለውጠው ፋሲል ከነማን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ምን ያህል ያስጉዙታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።