የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረጉ 2 ጨዋዎች ቀጥሎ ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
በ9 ሰአት በመጠነኛ የዝናብ ካፍያ የተጀመረው የደደቢት እና የንግድ ባንክ ጨዋታ ብዙም የተመልካችን ቀልብ ሳይገዛ በባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የሀምራዊዎቹን የድል ግብ ኤልያስ ማሞ በ8ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ ንግድ ባንክ ድሉን ተከትሎ በ38 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡናን ተጠግቷል፡፡
በ11፡30 ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን አስፍቷል፡፡ ፈረሰኞቹ በሀዋሳ ከነማ ተጫዋቾች ጭብጨባ ታጅበው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን አንደኛው አጋማሽ ካለ ግብ ተጠናቋል፡፡ በ2ኛው አጋማሸ 48ኛው ደቂቃ በሃይሉ አሰፋ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አዳነ ግርማ ወደ ግብ ቀይሮ ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል፡፡ አዳነ በ64ኛው ደቂቃ 2ኛውን ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ ከግብ ርቆ የሰነበተው ኡመድ ኡኩሪ በ67ኛው እና 88ኛው ደቂቃ አከታትሎ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን ለ40 ድል አብቅቷል፡፡ ኡመድ ዛሬ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 15ኛ እና 16ኛ የሊግ ግብ ሆነው ተመዝግበውለታል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉ ነገ በሚደረጉ 5 ጨዋታዎች ሲቀጥል አዲስ አበባ ላይ በ9 ሰአት ኢትዮጵያ መድን ከ መብራት ኃይል ፣ 11፡30 ላይ መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ ጫወታሉ፡፡ ክልል ላይ ሐረር ሲቲ አርባምንጭ ከነማን ፣ ሙገር ሲሚንቶ ሲዳማ ቡናን እንዲሁም ዳሽን ቢራ ኢትዮጵያ ቡናን በተመሳሳይ 9፡00 ላይ ያስተናግዳሉ፡፡