ባህር ዳር ከተማዎች ያለፈውን አንድ ዓመት ጥሩ ግልጋሎት የሰጣቸውን የመስመር አጥቂ ውል ማራዘማቸው ታውቋል።
በአሰልጣኝ ደግአረጋል ይግዛው እየተመሩ የአንደኛው ዙር ውድድራቸውን በሃያ ስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት የጣና ሞገዶቹ የመስመር አጥቂያቸውን ወንደሰን በለጠ ውል ማራዘማቸው ታውቋል።
የእግርኳስ ህይወቱን በዳንግላ ከተማ፣ ጀምሮ በኋላም በአውስኮድ እና ባቱ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው ወጣቱ የመስመር አጥቂ ባሳለፍነው ዓመት ነበር ባህር ዳር ከተማን ተቀላቅሎ የነበረው። የውል ዘመኑ በዚህ አጋማሽ መጠናቀቁን ተከትሎ እርሱን በቡድኑ ለማስቀረት ድርድር ያደረገው ቡድኑ በመጨረሻም ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በክለቡ የሚቆይበትን ስምምነት መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ወጣቱ አጥቂ በዘንድሮ ዓመት በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ለቡድኑ ሦስት ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወቃል።