የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የማጣራት ሂደቱ ሲጠናቀቅ የሚገኙ ነገሮች በሙሉ በዝርዝር ይፋ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ከሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነውን የክለቦች እና የተጫዋቾች ቅጣት በተመለከተ እየተሰጠ በሚገኘው ማብራሪያ የሊጉ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ቅጣቱን በቁርጠኝነት ከማስፈፀሙ ጋር ተያይዞ የሰጡትን ሀሳብ ቀድመን ያጋራን ሲሆን ሰብሳቢው በምርመራው ሂደት የተገኙ ግኝቶችን በሙሉ ይፋ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።
በማጣራቱ ሂደት ከኢንሳ ጋር የሚሰሩ ስራዎች በርካታ በመሆናቸውና ተቋሙ ደግሞ እንደ ሀገር ብዙ ስራ ያለበት ስለሆነ የማጣራት ሂደቱን አራዝሞታል ካሉ በኋላ ካሉት ሀገራዊ ስራዎች ጎን ለጎን የእኛም ጉዳይ ከፍተኛ ስለሆነ እና እግርኳስ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በማሰብ ማጣራቱ እንዲፋጠን ተደርጎ ሰኞ የወጣው ቅጣት እንዲወሰን ተደርጓል ብለዋል። ከጉዳዩ ውስብስብነት መነሻነት በትኩረት ቀጣይ የአስራ ስምንቱም ክለቦች እንቅስቃሴ ማጣራት ተደርጎበት የሚገኙ ግኝቶችም ይፋ እንደሚደረጉ አብራርተዋል።
