‹‹ ኮከብ ተጫዋች መባል አያስጨንቀኝም ›› በኃይሉ አሰፋ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዘመኑ የቻምፒዮንነት ጉዞ ቁልፍ ሚና የነበረው በኃይሉ አሰፋ በግሉ ለ3ኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ አንስቷል፡፡ ፈጣኑ የመስመር አማካይ ከዛሬው ጨዋታ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው አስተያየት የድላቸውን ምስጢር ያብራራል፡፡

‹‹ በ2007 ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈናል፡፡ ጥሩ አጀማመር ማድረግ አልቻልንም ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር ክለቡ በድክመቶቹ ላይ ሰርቷል፡፡ እኛም ድክመቶቻችንን እያረምን እና ከጨዋታ ጨዋታ እየተሸሻልን ለቻምፒዮንነት በቅተናል፡፡ ››

በውድድር ዘመኑ ባሳየው ድንቅ አቋም የአመቱ ኮከብ ሊሆኑ ከሚችሉ ተጫዋቾች ግንባር ቀደም ግምት የተሰጠው በኃይሉ ኮከብነት ብዙም እነደማያስጨንቀው ይናገራል፡፡

‹‹ በግሌ ኮከብ ተጫዋች መባል አያስጨንቀኝም፡፡ ትልቁ ነገር ከቡድኑ ጋር ዋንጫ ማንሳት ነው፡፡ ወደ ኢንተርናሽናል ውድድር መመለስም ችለናል፡፡ የሚያስጨንቀኝ የግል ክብር ሳይሆን የክለቡ ነው፡፡ ቅድሚያ መሰጠት ያለበትም ለክለቡ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በቀጣዩ አመት 80 አመት የሚሞላው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉ አስደስቶኛል፡፡

‹‹ የዋንጫ ባለቤት መሆናችን ለክለቡ ብቻ ሳይሆን በግሌም አንድ ደረጃ ከፍ የምልበት ነው፡፡ የስኬቴ ምስጢር ከጉዳት ነፃ መሆኔ እና ሁልጊዜም ጠንካራ ልምምድ ማድረጌ ነው፡፡ ››

በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ግማሽ በብራዚላዊው አሰልጣኝ ኔይደር ዶሳንቶስ ስር ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደወትሮው ጨዋታዎችን ማሸነፍ ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ከአሳልጣኙ ስንብት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ ፋሲል እና ዘሪሁን እንደተለወጠ በሃይሉ ያምናል፡፡

‹‹ ፋሲል እና ዘሪሁን በቡድናችን ያመጡት ትልቅ ነገር መግባባት ነው፡፡ ከውጪ አሰልጣኞች ጋር መግባባት እና አሰለጣጠናቸውን መረዳት አስቻጋሪ ነው፡፡ ከነ ፋሲል በፊት ቡድኑ ይከተለው የነበረው ታክቲክ ጥሩ ያልነበረ ከመሆኑም በላይ ቡድናችን የወጥነት ችግርም ነበረበት፡፡ ከአሰልጣኝ ለውጡ በኋላ ቡድኑ ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ የውድድር ዘመኑንም በዋንጫ አጠናቋል፡፡ ››

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን ቢሆንም ቀሪዎቹን ጨዋታዎቸን አሸንፈው በድል ዋንጫውን ለመሳም እንደሚፈልጉ ተናግሯል፡፡

‹‹ ቻምፒዮንነታችንን ብናረጋግጥም ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ማሸነፍ እንፈልጋለን፡፡ በታሪካዊው ክለብ ውስጥ ሽንፈት ቦታ የለውም፡፡ የመጨረሻውን የደደቢት ጨዋታ አሸንፈን በድል ዋጫውን ማንሳት እንፈልጋለን፡፡ ››

በመጨረሻም ቡድኑ ባሳለፈው ውጣ ውረድ የተሞላበት የውድድር ዘመን ከጎናቸው የቆመውን ደጋፊ አመስግኗል፡፡

‹‹ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በምንሄድበት ሁሉ የሚደግፈንን ደጋፊ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ››

ያጋሩ