ፕሪሚየር ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊግ ቻምፒዮንነቱን አረጋገጠ

በኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ 24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከነማን 3-1 አሸንፎ የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮንነቱን አረጋግጧል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስን የአሸናፊነት ግቦች በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አዳነ ግርማ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምንት እንዲሁም አማካዩ ምንተስኖት አዳነ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የአርባምንጭን ብቸኛ ግብ ፀጋዬ አበራ ከመረብ ሲያሳርፍ ተሸመ ታደሰ በመጀመርያው አጋማሽ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አምክኗል፡፡

ድሉን ተከትሎም 2 ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ጨዋታ እየቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከጨዋታው በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከደጋፊዎች ጋር ደስታቸውን የገለፁ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቻምፒዮንነታቸው የልፋታቸው ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ዋንጫውን በማግኘታችን ደስ ብሎኛል፡፡ ቡድኖች ቻምፒዮን የሚሆኑት ቡድኖች ለፍተው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እኛም ለፍተን አሳክተናል፡፡ በሁለተኛው ዙር 1ኛው ዙር ላይ የነበሩብንን ድክመቶች አርመን ቻምፒዮን ለመሆን በቅተናል፡፡

‹‹ እንደ ቡድን በመጫወት አላማችንን አሳክተናል፡፡ ለድላችን መሳካት ሁሉንም ተጫዋች አመሰግናለሁ፡፡ ደጋፊዎቻችን በኛ ደስተኛ ሆነው ሲጨፍሩ ማየታችን ያስደስተናል፡፡ በመጨረሻም ደጋፊዎቻችን የሚፈልጉትን አግኝተዋል፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ›› ብለዋል፡፡

ያጋሩ