ጌታነህ ከበደ በዊትስ መውጫ በር ላይ ቆሟል

 

የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ እና ደደቢት የአጥቂ መስመር ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ከቢድቭስት ዊትስ ጋር የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን ከደቡብ አፍሪካ የሚወጡ ዘገባዎች ጠቁመዋል። ጌታነህ በብሉምፎንቴይኑ ክለብ ለተጨማሪ አንድ አመት የሚያቆየው ኮንትራት ቢኖረውም ክለቡ ተጫዋቹን ለማቆየት ፍላጎት እንደሌለው ነው የተነገረው።

ጌታነህ በ2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በደደቢት ባሳየው ድንቅ አቋም እና ለሰውነት ቢሻው የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጤታማነት ባደረገው አስተዋፅኦ ምክኒያት በበርካታ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ዕይታ መግባት ችሎ ነበር። ቢድቨስት ዊትስ ከተቀላቀለ በኋላም ባደረጋቸው የመጀመሪያዎቹ 5 ጨዋታዎች 4 ግቦችን በማስቆጠር ያሳየው ጥሩ አጀማመር ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት መዝለቅ አልቻለም። ዘንድሮ ጌታነህ ለዊትስ 10 ጨዋታዎችን ብቻ አድርጓል፤ ከነዚህም ውስጥ በግማሹ የቋሚ ተሰላፊነትን ዕድል አግኝቶ 3 ግቦችን አስቆጥሯል።

ቢድቨስት ዊትስ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን የውጪ ዜጋ ያላቸው ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት እያደረገ ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ሊግ ባስቀመጠው የ5 የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ኮታ ምክኒያት ከጌታነህ ከበደ በተጨማሪ የ2012 የቢቢሲ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ስያሜን አግኝቶ የነበረው ዛምቢያዊው ክሪስቶፈር ካቶንጎ ክለቡን እንደሚለቅ ተገምቷል። በክለቡ የሚገኘው ሌላው ኢትዮጵያዊ ፍቅሩ ተፈራ የደቡብ አፍሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ስላለው እንደ የውጪ ዜጋ ተጫዋች አይመዘገብም።

ዊትስ ለሱዳኑ ኤል ሜሪክ በመጫወት ላይ የሚገኘው ኬንያዊ አጥቂ አላን ዋንጋ የጌታነህ ምትክ አድርገው ማስፈረም የሚፈልጉ ሲሆን ዋንጋ ከሜሪክ ጋር ያለው ኮንትራት በሰኔ ወር የሚጠናቀቅ መሆኑ ለዝውውሩ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል። አላን ዋንጋ በ2014 የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የኬንያው ሊዎፓርድስ ከመከላከያ ጋር አዲስ አበባ ላይ ባደረገው ጨዋታ ሁለት ግቦች በማስቆጠር ክለቡ 2-1 እንዲያሸንፍ ማስቻሉ ይታወሳል።

ያጋሩ