ዮሃንስ ሳህሌ አዲሱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ፡፡

የደደቢቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ አዲሱ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ፕላኔት ስፖርት ዘግቧል፡፡

ከማርያኖ ባሬቶ ጋር በስምምነት የተለያየው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን መምረጡ ተነግሯል፡፡ ምርጫውን ሲያካሂድ ነበርው የእግርኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ክፍል ለመጨረሻ ዕጩነት ዮሃንስ ሳህሌን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፋሲል ተካልኝ እና የአዳማ ከነማው አሸናፊ በቀለ አቅርቦ ነበር፡፡ የቴክኒክ ክፍሉ ለምርጫው መመዘኛ መስፈርት አሰልጣኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ያላቸው ውጤት እና የትምህርት ደረጃቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቢያንስ ከ80ሺህ-100ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ይከፈላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከዮሃንስ ጋር ካልተስማማ በምትካቸው ፀጋዬ ኪዳነማርያም የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ ምንጮች ተቁመዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ በተጫዋችነት ዘመናቸው ለራስ ሆቴል፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጫወት አሳልፈዋል፡፡ በ1975 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ዋንጫን ከጊዮርጊስ ጋር አሸንፈዋል፡፡ በአሜሪካም ለተለያዩ ክለቦች ተጫውተው አሳልፈዋል፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው በአሜሪካ የተለያዩ የኮሌጅ ክለቦችን አሰልጥነዋል፡፡ የደደቢት እግርኳስ ክለብን በአሰልጣኝነት እንዲሁም በቴክኒካል ዳይሬክተርነት ሰርተዋል፡፡ አሰልጣኙ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተርም ነበሩ፤ በተጨማሪም አሰልጣኙ የአሜሪካ ዜግነት አላቸው፡፡ እግርኳስንም በአሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሆላንድ እና ጀርመን ተምረዋል፡፡

ያጋሩ