“ክለቡ ውጤት በማጣቱ ምክንያት የፈጠረብኝ ጫና የለም” የደደቢቱ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 1ኛ ዙር ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4 ነጥብ ርቆ በ2ኝነት ያጠናቀቀው ደደቢት በሁለተኛው ዙር ውጤት ከድቶታል፡፡ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎችም 1 ብቻ አሸንፎ ደረጃው ወደ 6ኛ አሽቆልቁሏል፡፡

ከትላንቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት በኀላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደደረጉት የክለቡ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ግን በጫና ውስጥ እንደማይገኙ ተናግረዋል፡፡
 
በ2ኛው ዙር ውጤት ርቋችኋል፡፡ መንስኤው ምንድነው?

የተጨዋቾች ተደጋጋሚ ጉዳት ፣ የቅጣት መደራረብ ፣ የስብስቡ ጥልቀት ፣ ከብሄራዊ ሊጉ ያመጣናቸው ተጫዋቾች በቶሎ አለመዋሃድ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ለውጤቱ መጥፋት መንስኤ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
 
በሊጉ ጫና ውስጥ ከሚገኙ አሰልጣኞች አንዱ ነህ… ይህ ተሰምቶሀል?

ለምን ጫና ይሰማኛል:: አንደኛ ውጤቱ የኔ ብቻ ሳይሆን የሙሉ የቡድኑ ነው። ውጤት ሲመጣም ውጤት ሲጠፋም እንደዚህ ነው ። በእግር ካስ ደግሞ ያለ ነገር ነው ። እኛ አንደኛው ዙር ላይ ጥሩ ውጤት ነበረን፡፡ አሁን ሁለተኛው ዙር ላይ ትንሽ ወደታች ተንሸራተናል ፣ ክለቡም እንደሚፈልገው አልሆነም፡፡ በዚህም ቁጭት ይሰማኛል፡፡ ከዛ በተረፈ ግን በኔም በክለቡም ላይ የሚፈጥረው ጫና የለም፡፡
 
ከዋንጫው ፉክክር ወጥተናል ብላቹ ታስባላቹ?

እ. . . ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ካየነው ነጥቡ በጣም እየሰፋ መጥቷል፡፡ ከኋላ የነበሩት ወደፊት እየመጡ ነው፡፡ እግር ኳስ እንዲህ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮዽያ ቡና 9ኛ ነበር ፤ አሁን ደግሞ ሁለተኛ መጥቷል፡፡ እነዚህን ነገሮች ሲታዩ እኛም ነገ ወደ ነበርንበት እንመለሳለን ብዬ አስባለው።
 
የውድድር ዘመኑ መጨረሻ ግባችሁ ምንድን ነው?

አሁን የምንሰራው ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ነው፡፡ በአንደኛው ዙር ላይ የነበረንን ምርጥ አቋም መመለስና የውጤት መንገዳችንን ፈልገን ማግኘት ነው ዋናው ስራችን የሚሆነው፡፡ በየጨዋታው የሚደርስብን አላስፈላጊ ነገሮች እንዳሉ ሆነው ቁጭ ብለን ችግሮቻችንን ፈትሸን እንደገና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ተነጋግረናል ።
 
የወደፊት ቆይታህ?

እንግዲህ የወደፊቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ አሁን ግን ክለቡ ውጤት በማጣቱ ምክንያት የፈጠረብኝ ምንም አይነት ጫና የለም፡፡ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ቁጭ ብለን ተነጋግረናል ክለቡ ውስጥ ያለው አሰራር ይህ ነው ።

Leave a Reply