አሚን አስካር ለአዲሱ ክለቡ ግብ አስቆጠረ

ኢትዮጵያዊው አሚን አስካር ትላንት ምሽት በቲፔሊጋን (የኖርዌይ ሊግ) ክለቡ ሳርብስቦርግ ኦድን 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ 2ኛዋን ግብ በ34ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎም የአሚን ክለብ ሳርብስቦርግ ከ5 ጨዋታ 8 ነጥቦች በመሰብሰብ በ2015 የኖርዎይ ሊግ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የ29 አመቱ የመስመር አጥቂ 3 የውድድር ዘመናት ያሳለፈበትን ብራን ለቆ ለሌላው የኖርዌይ ሊግ ክለብ ሳርብስቦርግ በውሰት ውል የፈረመው በማርቸ ወር 2015 ሲሆን እስካሁን 5 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ትላንት ያስቆጠራት ግብም በአዲሱ ክለቡ የመጀመርያው ሆና ተመዝግባለታለች፡፡

ሙሉ የጨዋታ ዘመኑን በኖርዌይ ያሳለፈው አሚን አስካር በእግርኳስ ዘመኑ በክለብ እግርኳስ 302 ጨዋታችን አድርጎ 54 ግቦችን ከመረብ ቢያሳርፍም አንድም ኢንተርናሽናል ጨዋተ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ አላደረገም፡፡ በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ዘመን ለብሄራዊ ቡድናችን ተመርጦ በተገቢነት ጉዳይ ሳይጫወት መቅረቱ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በስካንዴኔቭያ የሚገኘው ሌላው ኢትዮጵያዊ የሱፍ ሳላህ በስዊድን ሁለተኛ ዲቪዥን (ሱፐርታን ሊግ) ክለቡ ኤ.ኤፍ ሲ. ኡቲስከንን 2-0 በረታበት ጨዋታ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ታዳጊው ዮናታን ጌታቸው ደግሞ ለስዊድኑ ሂልስንቦርግ ዋናው ቡድን መጫወት ጀምሯል፡፡: የ18 አመቱ ዮናታን በአዲሱ የ2015 የውድድር ዘመንም ለክለቡ 3 ጨዋታዎችን (2 በመጀመርያ ተሰላፊነት) አድርጓል፡፡

ያጋሩ