ዮሐንስ ሳህሌ የዋልያዎቹ ስራቸውን ሚያዝያ 26 በይፋ ይጀምራሉ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በአዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቅጥር እና ተያያዥ ጉዳዮች ጉዳይ ላይ ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አሰልጣኙ ሚያዝያ 26 / 2007 ስራ የሚጀምሩ ሲሆን ወርሃዊ ደሞዛቸውም 75ሺህ ብር ይሆናል፡፡

በዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት የላከው መግለጫ ይህንን ይመስላል፡፡

‹‹

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ሰኞ ሚያዝያ 26/ 2007 ስራ ይጀምራል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን-የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ በመሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት የተመረጠው ዮሐንስ ሳህሌ ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም የማሰልጠን ስራውን በይፋ ይጀምራል፡፡ ዮሐንስ ሳህሌ የብሔራዊ ቡድኑን ዋና አሰልጣኝነት እና ታላቅ ሃገራዊ ሃላፊነት እንዲረከብ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በፌደሬሽኑና በአሰልጣኙ መካካል የተካሄዱት ተከታታይ ውይይቶች በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቁ በኋላ ፌዴሬሽኑና አሰልጣኙ በተፈራረሙት የቅጥር ውል መሰረት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከሰኞ ሚያዝያ 26/ 2007 ጀምሮ ዋሊያዎቹን የማሰልጠን ሃላፊነቱን ይረከባል፡፡ ዮሐንስ ሳሕሌ ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ የተሰጠውን የማሰልጠን ሃላፊነት እሁድ ሚያዘያ 25/2007 እንሚያጠናቅቅና በክብር እንደሚሰናበት የሚጠበቅ ሲሆን፤ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ክለብ ያሳየው ፍጹም ቀናነት የተሞላውና ብሄራዊ ግዴታን የማስቀደም ተባባሪነት አሰልጣኙ በፍጥነት ስራውን እንዲጀምር አመቺ ሆኖለታል፡፡

ፌዴሬሽኑና አሰልጣኙ የተፈራረሙት የቅጥር ውል ዋና ዓላማ እ.አ.አ. በ2017 ጋቦን በምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ዋሊዎቹ ከተደለደሉበት ምድብ 10 ከስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎች ውስጥ ወደ ዋናው ውድደድር ለማለፍ የሚያስላቸውን ነጥብ በማግኘት የ31ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊነታቸውን በማረጋጋጥ ላይ ይመሰረታል፡፡በቻን 2016 እና በሴካፋ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ውድድሮችም አመርቂ ውጤት ይጠበቃል፡፡

በውል ስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እ.አ.አ በ2017ዓ.ም ጋቦን በምታስተናገደው 31ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ ተካፋይ ለመሆን ከቻለ የአሰልጣኝ ዮሐንስ የስራ ዘመን እ.አ.አ እስከ ኤፕሪል 2017 ዓ.ም ድረስ እንደጸና ይቆያል፡፡ የብሔራዊ ቡድኖች መጠናከር ልዩ ትኩረት የሚሻ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን በማማንም ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኝ ዮሐንስ 75 000 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ይከፍላል፡፡ተሽከርካሪ ከሾፌር ጋር እንዲሁም ባለመስመር የሞባይል ስልክና የጤና ኢንሹራንስ ከማሟላት በተጨማሪም ውጤትን መሰረት ያደረገ ማበረታቻ ይሰጣል፡፡

የኢትጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ረዳትና የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ቅጥር በቅርቡ የሚካሄድ ሲሆን አሰልጣኝ የሐንስ ሳህሌ የረዳቶቹን ማንነት በአጭር ጊዜ ወስጥ ለፌዴሬሽኑ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡የቴክኒክና ልማት ብሔራዊ ኮሚቴ የሚሰጠውን አሰተያያት መነሻ በማድረግም የረዳቶቹ ቅጥር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደሚጸድቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ፌዴሬሽኑና አሰልጣኙ የደረሱበትን ስምምነትና የተፈራረሙትን የቅጥር ውል በተመለከተም ሰሞኑን ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡

››

ያጋሩ