ፕሪሚየር ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ሲያጠናክር ደደቢት የቻምፒዮንነት ፉክክሩን ተቀላቅሏል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት 5 ጨዋታዎች ዛሬ በክልል እና አዲስ አበባ ተካሂደው የዋንጫውን ጉዞ እና የወራጁን ክለብ ማንነት በመጠኑ የሚጠቁሙ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ወደ አሰላ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለሜዳው ሙገር ሲሚንቶን 2-1 አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ወሳኝ የድል ግቦች ከመረብ ያሳረፉት ብሪያን ኡሞኒ እና ምንተስኖት አዳነ ናቸው፡፡ ድሉን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በ42 ነጥቦች ሊጉን ከተከታዩ ሲዳማ በ4 ነጥቦች ርቆ ሲመራ ሙገር በበኩሉ በ19 ነጥቦች ላይ በመርጋት ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል አደብዝዞታል፡፡

በሲዳማ ደርቢ ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በደጋፊው ፊት 1-0 ተሸንፏል፡፡ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ሽንፈት ያስተናገደው ሲዳማ በ38 ነጥቦች 2ኛ ደረጃን እንደያዘ ቀጥሏል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ንግድ ባንክን የገጠመው ደደቢት 3-0 አሸንፏል፡፡ የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው በዚህ ግጥሚያ ናይጄርያዊው ሳሚ ሳኑሚ ፣ በረከት ይሳቅ እና ሽመክት ጉግሳ የደደቢትን የድል ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ሳኑሚ የውድድር ዘመኑን 14ኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን ዛሬ በምግብ መመረዝ ምክንያት ወደሜዳ ያልገባው ፊሊፕ ዳውዚን የግብ መጠን ተጋርቷል፡፡ ደደቢት ነጥቡን ወደ 34 ከፍ ያደረገ ሲሆን ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 5 ያጠባል፡፡

ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ወልድያን 1-0 አሸንፏል፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ክለቡን የተቀላቀለው ቶጓዊው ኤዶም ሆሶውሮቪ ግብ በመውረድ ስጋት ውስጥ ያለውን ክለብ ተስፋ ሲያለመልም የወልድያን የመውረድ ጉዳይ አይቀሬ አድርጎታል፡፡

አመሻሽ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ወላይታ ድቻን ያስተናገደው መከላከያ በመጨረሻ ደቂቃ በተገኘች የማሸነፍያ ግብ ጣፋጭ ድል አስመዝግቧል፡፡ መከላከያ በሙሉአለም ጥላሁን ግብ 1-0 ሲመራ ቆይቶ አላዛር ፋሲካ ድቻን አቻ አድርጓል፡፡ በ90ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ግብ አስቆጥሮ ጦሩን ወደ አሸናፊነት መርቷል፡፡ መከላከያ ከአስደንጋጩ የተክለወልድ ህልፈት በኋላ የመጀመርያ ድሉን ዛሬ አሳክቷል፡፡

አርብ እና ቅዳሜ በተደረጉት ሌሎች ጨዋታዎች አዳማ ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን ፣ ኤሌክትሪክ አርባምንጭን በተመሳሳይ 1-0 መርታታቸው ይታወሳል፡፡

 

 

ያጋሩ