ፕሪሚየር ሊግ ፡ ባንክ ከ ሀዋሳ ከነማ አቻ ተለያዩ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄዱ የ23ኛ ሳምንት 2 ጨዋታዎች ደደቢት ድል ሲቀናው ንግድ ባንክ ከሀዋሳ አቻ ተለያይቷል፡፡

በ9 ሰአት ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ ሀዋሳ ከነማ ጋዲሴ መብራቴ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ባስቀቆጠራት ግሩም ግብ 1-0 መምራት ቢችሉም ከምግብ መመረዝ ህመም የተመለሰው ፊሊፕ ዳውዚ በግንባሩ በመግጨት ንግድ ባንክ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል፡፡ ግቧ ለፊሊፕ 15ኛ ስትሆን ደደቢት ጨዋታ ከማድረጉ በፊትም ከሳኑሚ እኩል የኮከብ ግብ አግቢነቱን ለመምራት አስችሎት ነበር፡፡

ከጨዋታው በኋላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም የስብስብ ጥልቀት እና የተከላካዮች ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ የተጫወትነው ከጠንካራ ተጋጣሚ ጋር ነው፡፡ ጨዋታውን ለማሸነፍ በፍላጎት ተጫውተን ነበር፡፡ ነገር ግን የፈጠርናቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በፊሊፕ ላይ ጥገኛ መሆናችን እና የስብስባችን ጥልቀት ማነስም አስተዋፅኦ አድርጎብናል፡፡ ነገር ግን ከአዳማው ሽንፈት በኋላ አንድ ነጥብ ማግኘታችን ለኛ መልካም ነው፡፡››

የሀዋሳ ከነማው ውበቱ አባተ በበኩላቸው ሀዋሳ ከነማ አንድ ነጥብ በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ባንክ ጠንካራ ቡድን በመሆኑ 1 ነጥብ ማግኘታችን አስደስቶኛል፡፡ የትኩረት ማጣት ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘን እንዳንወጣ አድርጎናል፡፡ ቡድኑን ከተረከብኩ ጀምሮ የሚታይ መሻሻል እያሳየን በመምጣታችን በእርግጠኝነት ዘንድሮ ከሚወርዱት 2 ክለቦች አንዱ አንሆንም›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

 

 

ያጋሩ