የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋዜጣዊ መግለጫ

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ለሦስተኛ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደውና በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚገኙ ተጫዋቾችን ለሚያሳትፈው ውድድር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ይህንን አስመልክቶም የቡድኑ አሰልጣኝ አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ ረቡዕ ከሰዓት መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም ስለቀጣይ ግላዊ እቅዳቸው፣ ስለ ተጫዋቾች ምርጫና አመራረጡ፣ ከውድድሩ ምን መጠበቅ እንዳለበት ከጋዜጠኞች ጋር በጥያቄና መልስ መልክ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ስለ ዝግጅታቸው

እንደዚህ ቀደሙ በርካታ ተጫዋቾችን ይዘን ዝግጅት መጀመር አልቻልንም፣ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከካፍ የመጣው መመሪያ ነው ተጫዋቾቹ ቶሎ የህክምና ምርመራ ማድረግ ስለነበረባቸው እና እሱም በጊዜ ተጠናቆ መግባት ስለነበረበት ያን ማድረግ (በዛ ያሉ ተጫዋቾችን ማሳተፍ) ተቸግረናል በተቻለ መጠን ግን ጥሩ የዝግጅት ጊዜ አድርገናል ፡፡

ስማቸው ከጊኒ ብ/ቡድን አሰልጣኝነት ጋር ስለመያያዙ

የውጪ ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖች ጋር በተያያዘ የተወራው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ እርግጥ አሰልጥንልን ብለው የጠየቁ በርካታ ቡድኖች አሉ እኔ ግን ማንንም አልጠየኩም፡፡ ነገር ግን ከብ/ቡድኑ ከተለየው በኋላ በቀጣይ በርካታ ውድድሮችን እና ስፖርተኞን ለማየት እና ለመመልመል እቅድ ይዣለው፡፡

ስለ ዳዊት እስጢፋኖስ

ከዳዊት ጋር የግል ችግር የለብኝም፤ ወቅታዊ አቋሙም ጥሩ እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን እንዳልኩት ምርጫው የተከናወነው በየቦታው በሚታየው ክፍተት ላይ ነው፡፡ በእርሱ ቦታ ላይ ደግሞ ልጆች አሉ፡፡ እሱ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ቢሆን ኖሮ ካለብኝ እጥረት አንፃር እመርጠው ነበር፡፡

ዋልያዎቹ ዛሬ ረፋድ ቀለል ያለ ልምምድ ካደረጉ በኋላ እርስ በእርስ ለሁለት በመከፈል ጨዋታ አድርገዋል፡፡

አንደኛው ቡድን በግብጠባቂነት ጀማል ጣሰው፤ እንዲሁም ሥዩም፣ ደጉ፣ ቶክ፣ አበባውን በተከላካይነት እንዲሁም ታደለ፣ ምንተስኖት፣ ሰለሀዲንና ፋሲካን በአማካይነት ማናዬ እና ኤፍሬምን ደግሞ በፊት ተሰላፊነት ይዞ ነበር፡፡

ሌላኛው ቡድን ላይ ደግሞ ግብ ጠባቂ ደረጄ (ግማሽ ላይ በታሪኩ ተቀይሯል) ዓይናለም፣ ቢያድግልኝ፣ አሉላ እና ብርሀኑን በተከላካይነት፣ በአማካይነት ደግሞ አሥራት፣ አዳነ፣ ምንያህል እና በኃይሉን ይዞ ነበር። ፊት ላይ ደግሞ ኡመድ እና ዳዊትን አድርጎ ነበር፡፡

ምንጭ – ኑራ ኢማም


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ