የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀምራል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ የ2009 የውድድር ዘመን ከተጀመረ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜም በሳምንቱ አጋማሽ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

በዛሬው እለት 2 ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋሉ፡፡ 3 ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ በድንቅ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ 09:00 ላይ ይደረጋል፡፡ መጥፎ የውድድር ዘመን ጅማሬውን ካሻሻለ በኋላ ያለፉት ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያልቻለው ንግድ ባንክ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ፤ መከላከያ እያሳየ ባለው ድንቅ አቋም ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ ጥሩ ፉክክር ይጠበቃል፡፡

11:30 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ ይፋለማሉ፡፡ ሁለቱ የሊጉ አዲስ ቡድኖች የውድድር ዘመናቸው በተለያየ አቅጣጫ እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ፋሲል በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪዎቹ በጥቂት ነጥቦች አንሶ ሲቀመጥ አአ ከተማ በተከታታይ 4 ጨዋታዎች ተሸንፎ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይገኛል፡፡

የሊጉ 5 ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ የሊጉ መሪ ደደቢት ወደ አርባምንጭ ተጉዞ አርባምንጭ ከተማን ይገጥማል፡፡ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ09:00 ይጫወታል፡፡ ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡና ከ ሲዳማ ቡና እንዲሁም ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ነገ 09:00 ላይ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ነገ 11:30 ላይ ይጀምራል፡፡

አርብ በሚደረገው ብቸኛ ጨዋታ ወልድያ መልካ ቆሌ ላይ በሚያደርገው የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ ወልድያ ከዚህ በኋላ በሊጉ የሚያደርጋቸው የሜዳ ጨዋታዎችን በአዲሱ የሼኽ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡


ሶከር ኢትዮጵያ በድረገጿ ዛሬ የሚደረጉትን ሁለቱንም ጨዋታዎች በቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት ወደ እናንተ ታደርሳለች፡፡ ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ ደግሞ ዛሬ አመሻሽ ከ11:00-12:00 በአባይ ኤፍ ኤም 102.9 መከታተል ትችላላችሁ፡፡

Leave a Reply