መከላከያ 1-2 አርባምንጭ ከተማ | የአሰልጣኞች አስተያየት 

ጳውሎስ ፀጋዬ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” የዛሬው ጨዋታ እንዳያችሁት ጥሩ ነበር ፤ ከጨዋታው የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል፡፡”

“ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳችን ውጪ ወደ ድሬዳዋ ተጉዘን በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ ይዘን ተመልሰናል፤ ዛሬም ሶስት ነጥብ ይዘን ወጥተናል፡፡  አሁን ላይ ሆነን ከዚህ ቀደም የነበሩብንን ችግሮች አስወግደን እንዳያችሁት ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ተበልጠናል ፤ እኛ ውጤቱን አስጠብቀን ለመውጣት ስላሰብን በመልሶ ማጥቃት ላይ ለመጫወት ነበር የፈለግነው ያንንም አሳክተን መውጣት ችለናል፡፡”

በቀጣይ ቡድኑ ስለሚኖረው ጉዞ

” ከዚህ በኃላ ወደ ኃላ ማለት የለም፡፡ አሁን ባለን ነገር እንቀጥላለን፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ በርከት ያሉ ኳሶችን አምክነናል እነዛን በማረም በቀጣይ ተፎካካሪ ለመሆን እንጫወታለን፡፡”

አዳዲስ ተጫዋቾች ስለመጠቀም

” ልምድ የሌላቸው ወጣት ተጫዋቾችን እያደፋፈርክ ካላጫወትካቸው በስተቀር በጣም ያስቸግራል፡፡ ወጣቶቹ በጣም ጥሩ ናቸው እስካሁንም ያልተጠቀምኳቸው ገና የምጠቀምባቸው ወጣቶች አሉ ፤ ከዚህ በኃላ አብዛኛውን ትኩረቴን ወጣቶች ላይ በማድረግ ልምድ ካላቸው ነባር ተጫዋቾች ጋር በማቀናጀት ጥሩ ነገር ለመፍጠር እንጥራለን፡፡”

ሻለቃ በለጠ ገ/ኪዳን – መከላከያ

ስለ ጨዋታው

“በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን ተመልክተናል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ያገኘናቸውን በርካታ የግብ እድሎች ብንጠቀም ኖሮ ነጥብ ይዘን ልንወጣ እንችል ነበር፡፡ ነገርግን ያባከናቸው ኳሶች ዋጋ አስከፍለውናል፡፡”

“በመጀመሪያው አጋማሽ አስቀድመን ግብ አስቆጥረን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር ያቀድነው ፤ ነገር ግን እግርኳስ የስህተት ጨዋታ ነው፡፡ በሰራናቸው የተወሰኑ ስህተቶች ልንቀደም ችለናል፡፡ ሆኖም ግን ቡድኔ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ከኃላ ተነስተን ለማሸነፍ ሞክረናል፡፡ በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ልንቀሳቀስ ችለናል፡፡”

” በቀጣይ ከፊት መስመር ላይ የሚታዮብንን የተወሰኑ ስህተቶች ቀርፈን ተሻሽለን ለመምጣት እንሞክራለን፡፡”

ስለ ተከላካይ ክፍላቸው መሳሳት

” በሊጉ ከሚጫወቱ ክለቦች ውስጥ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካላቸው ቡድኖች አንዱ የኛ ቡድን ነው፡፡ ከሌላው ለየት በሚል መልኩ የኛ ቡድን አጥቂው ብቻ ሳይሆን የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎችም ጭምር ግብ ያስቆጥራሉ ፤ ኳስ ለመጫወት ከማሰብ የተነሳ በሚሰሩ የትኩረት ማነስ ችግሮች ግብ እያስተናገድን እንገኛለን እንጂ በተከላካይ መስመራችን ላይ የብቃትም ሆነ የችሎታ ማነስ ችግር የለብንም ይህንንም ለማረም በቀጣይ ጠንክረን እንሰራለን፡፡”

2 Comments

  1. We are watching foot ball field like court to accuse referees on the pitch which is very bad to foot ball referees acused in the field of play us only in ethiopia which is very outdated rule abd regulation

    Sorry

Leave a Reply