የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ቢጥልም የሊጉን መሪነት ከአዳማ ተረክቧል

በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የቅዱሰ ጊዮርጊስ ክለብ ከ2 ወራት በፊት ህይወቱን ላጣው ክብረአብ ዳዊት ቤተሰቦች በእለቱ አምበል አዳነ ግርማ አማካኝነት የገንዘብ ስጦታ በማበርከት ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡ እጅግ ደማቅ በነበረ የደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታም ጥሩ የኳስ ፍሰት ታይቶበታል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሀዋሳ ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር፡፡ ኳስ ይዞ በመጫወት እና ወደ ግብ በመድረስም የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል፡፡ በርካታ የግብ እድሎች የፈጠሩ ሲሆን በጋዲሳ መብራቴ ፣ ጃኮ አረፋት እና ፍሬው ሰለሞን አማካይነት ያለቀላቸውን ኳሶች በተደጋጋሚ አምክነዋል፡፡

በ15ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሀንስ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ተቆጣጥሮ ከግራ ጠርዝ አክርሮ በመምታት ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላም ሀዋሳ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በፍሬው ሰለሞን ፣ ጃኮ አራፋት እና ጋዲሳ አማካይነት ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳ ከተማ በመጠኑ ተዳክሞ ሲስተዋል በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ እንቅስቃሴን አድርጓል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎችም ኳሶቸችን በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በመጣል ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በ68ኛው ደቂቃ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው አብድልከሪም ኒኪማ ያሻገረውን ኳስ ራምኬል ሎክ በቄንጠኛ ሁኔታ ቺፕ አድርጎ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን አቻ አድርጓል፡፡

ሀዋሳዎች ከአቻነቱ ግብ በኋላ ወደ መሪነታቸው ለመመለሰ ከግቧ ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ ፍሬው ሰለሞን በግል ጥረቱ እየገፋ ወደ ሳጥኑ በመግባት የሞከረውን የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም ጃኮ አራፋት ከጋዲሳ መብራቴ ሶስት ተመሳሳይ ኳሶችን በተመሳሳይ ቦታ ቢሻገርለትም ያልተጠቀመባቸው ኳሶች ሀዋሳ 3 ነጥብ ሊያሳካ የሚችልባቸው እድሎች ነበሩ፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ራምኬል ሎክ ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት በግምባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ነበር፡፡

ጨዋታው በርካታ የግብ ሙከራዎች ቢያስተናግድም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስን የሊጉ አናት ላይ አስቀምጦታል፡፡

ከጫወታው መጠናቀቅ በኃላ በቡድናቸው እንቅስቃሴ የተበሳጩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አሰልጣኝ ማርቲን ኖይን ሲቃወሙ ፤ አንዳንድ ደጋፊዎችም አሰልጣኙን ለመደብደብ ሲጋበዙ ተስተውሏል፡፡

1 Comment

  1. great thanks for your information i love you very much!!!!!!!!!!!!!!!!!!

Leave a Reply