የጨዋታ ሪፖርት | የመከላከያ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ያለግብ አቻ ተጠናቋል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት አአ ስታድየም ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው መከላከያ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ጨዋታውን አጠናቋል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ሹፌሮች ማህበር በጋራ እያከበሩት ባሉት የሹፌሮች ቀን መነሻነት እንደ ትላንትናዎቹ ጨዋታዎች ሁሉ የመከላከያ እና የሲዳማ ቡናም ጨዋታ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን በ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማሰብ ነበር የተጀመረው ።

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። ምንም እንኳን ብዙ የጎል አጋጣሚዎች ልንመለከት ባንችልም በቡድኖቹ መሀከል የነበረው የመሀል ሜዳ ፉክክር ያለጎል ለተጠናቀቀው አጋማሽ ጥሩ ድምቀት የሰጠው ነበር።

ጨዋታው እንደጀመረ ሲዳማዎች በፈጠሩት ጫና ያገኙት የማዕዘን ምት ተሻምቶ መከላከያዎች ሲያወጡት የሲዳማው አማካይ ትርታዬ ደመቀ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ አቤል ማሞ በቀላሉ ይዞበታል ።  ከዚህ በተጨማሪ በ14ተኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በግራ መስመር ይዞ በመግባት ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሞከረው እና በ28ኛው ደቂቃ ግሩም አሰፋ ከመሀል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ አዲስ አለም አበበ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት ኳስ በሲዳማዎች በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ ።

ባለሜዳዎቹ መከላካዮችም በተለይ ከሁለቱ መስመሮች በሳሙኤል ሳሊሶ እና ሳሙኤል ታዬ በሚነሱ ኳሶች ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል ። ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ካደረጋቸው ሙከራዎች መካከልም የግራ መስመር ተከላካዩ ቴውድሮስ በቀለ መስመሩን ይዞ ወደተጋጣሚው የመከላከል ወረዳ ከገባ በኋላ የሞከረው እና የጎሉን የጎን  መረብ ታኮ የወጣው ኳስ የሚጠቀስ ነው።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ጥሩ የተንቀሳቀሱት መከላከይዎች በ46ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ሳሊሶ እንዲሁም በ 51ኛው ደቂቃ በምንይሉ ወንድሙ ከረጅም ርቀት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ለአለም ብርሀኑ ሁለቱንም ኳሶች አድኗቸዋል ። ጨዋታውም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እየታየበት ቀጥሎ 59ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ ተገኝ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ግሩም ሰይፉ ለማውጣት ሲሞክር ኳሷ በተቃራኒው ወደጎል ሄዳ ግብ ከመቆጠሩ በፊት ለአለም ብርሀኑ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ለማረግ የተቃረበች ዕድል ነበረች ።

ጨዋታው በገፋ ቁጥር መከላከያዎች ወደፊት ገፍተው ለማጥቃት በሚያደርጉት ጥረት ኳስ በሚነጠቁበት ወቅት ፈጥነው ወደመከላከል ቅርፅ የመመለስ ከፍተኛ ችግር የታየባቸው ሲሆን በተደጋጋሚም በራሳቸው ሜዳ ላይ በሲዳማ አጥቂዎች እና የአጥቂ አማካዮች በቁጥር ሲበለጡ ተስተውሏል ። ያም ቢሆን ሲዳማዎች አዲስ ግደይ በሚገኝበት የቀኝ መስመር እድልተው ሚጫወቱት ሲዳማዎች በመስመር አማካዩ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ተሞክራ ወደውጪ ከወጣችው ሙከራ ውጪ በተጋጣሚያቸው የመከላከል ችግር ይፈጠሩ የነበሩ ስህተቶችን  ሊጠቀሙበት አልቻሉም ።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በዚህ መልኩ ፍፃሜውን አግኝቷል ። በጨዋታው ባገኙት አንድ አንድ ነጥብም ሀለቱም ቡድኖች በነበሩበት ደረጃ ማለትም ሲዳማ ቡና በ25 ነጥብ 4ኛ መከላከያ በ20 ነጥብ 8ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል ።

Leave a Reply