ባዬ ገዛኸኝ ከረጅም ጊዜ ጉዳት ተመልሷል

የመከለካከያ የፊት መስመር ተሰላፊ የሆነው ባዬ ገዛኸኝ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ ተመልሷል፡፡ ባዬ ለሰባት ወራት ያክል ከሜዳ ርቆ የነበረ ሲሆን ለጦሩ በሁለተኛው ዙር የፕሪምየር ሊግ ውድድር ጥሩ ነገር ለማሳየት እንደሚፈልግ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡

የቀድሞ የወላይታ ድቻ አጥቂ የጉዳት ግዜያቱን አስቸጋሪ ሲል ገልጿቸዋል፡፡ “በጉዳት ያሳለፍኩት ግዜ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ወደ ሰባት ወር ያክል በጉዳት ነው የቆየሁት፡፡ አሁን በጣም ተሸሎኝ በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለው፡፡” ይላል ባዬ፡፡

ባዬ አያይዞም መከላከያ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላለበት ጨዋታ በጥሩ መልኩ እንደተዘጋጁ ተናግሯል፡፡ “ጥሩ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ከባለፈው የተሻለ ነገር ለማስመዝገብ ጥሩ እየሰራን ነው፡፡”

በግብፁ ምስር ኤል ማቃሳ በቅድመ ማጣሪያው ተሰልፎ መጫወት የቻለው ባዬ ክለቡ ካለፈው ስህተቱ በሚገባ መማሩን ይናገራል፡፡ “ከባለፈው ጨዋታ የተማርነው ሁሌም ነገሮችን በሜዳችን ጨርሰን መሄድ እንዳለብን ነው፡፡ እዛ ሄደንም ተሸንፈን ነው የመጣነው፡፡ ጨዋታዎች እዚሁ ሜዳችን ላይ ገድለን መሄድ እንዳለብን ተምረናል፡፡”

ባዬ በሁለተኛው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዙር የተሻለ ነገር ለማሳየት እንዳለመ ተናግሯል፡፡ “ጨራሽ አጥቂ እንደመሆኔ በሁለተኛው ዙር የተሻለ ነገር ለማሳየት እጥራለው፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡

Leave a Reply