አቤል ማሞ እና ሳሙኤል ታዬ ስለኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታቸው ይናገራሉ

መከለካያ በ2017 ቶታል የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ዕሁድ 10፡00 ላይ የካሜሩኑን ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚን አዲስ አበባ ላይ ያስተናግዳሉ፡፡ 

ጦሩ በጥር ወር በፕሪምየር ሊግ በደረጃው መንሸራተትን ቢያሳይም በግል ብቃታቸው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ እና ሳሙኤል ታዬ የተሻሉ ነበሩ፡፡ አቤል ከጉዳት መልስ በመልከም አቋም ላይ ሲገኝ በአስደናቂ ሁኔታ የሚያመክናቸው ሙከራዎች ክለቡን ውጤት ይዞ እንዲወጣ እያስቻሉ ይገኛሉ፡፡ አማካዩ ሳሙኤል ከመስመር እየተነሳ በጥር ወር ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ አርብ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ዝግጅት ሲያደርጉ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ተጫዋቾቹን አናግራለች፡፡

” ያለነው ውድድር ላይ ስለሆነ እየተዘጋጀን ያለነኽ በስነ ልቦናው ላይ ነው” አቤል ማሞ

ስለዝግጅት

“ውድድር ላይ ስለሆንን የተለየ ዝግጅት አላደረግንም፡፡ በስነልቦና ረገድ ነው ብዙ ዝግጅት ለማድረግ ያሰብነው፡፡ ምክንያቱም ያለነው ውድድር ላይ ስለሆነ ንቁ ነን፡፡ ግማሹም ዙር ያለቀው ከሳምንት በፊት እንደመሆኑ መጠን አሁንም ወደ ውድድር ነው የምንገባው ስለዚህ የተለየ ዝግጅት የለውም፡፡”

ስለተጋጣሚያቸው ዮንግ ስፖርት

“አሁን ባለን መረጃ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሚጫወት ተጫዋች የለም፡፡ አሁን ያሉበት ደረጃ በእርግጥ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ከሜዳ ውጪ ሲጫወቱ ብዙ የማግባት እድል እንደሚፈጥሩ እና ሌሎች ስለእነሱ የተሻሉ መረጃዎች አሉኝ፡፡ ነገር ግን ከቡድን አጋሮቼ ጋር ሆኜ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ነው የምጥረው፡፡”

በጥሩ አቋም ላይ መገኘት

“ምን አለ መሰለህ ከጉዳት ስትመለስ ብዙ ግዜ ጠፍተህ ነው የምትመጣው፡፡ ያለህበትን ሁኔታ ደግሞ በአዕምሮ ተዘጋጅተህ ነው መምጣት ያለብህ፡፡ በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ ስለሆንኩ ያው የማውቀውን ስራ ነው እየሰራው ያለሁት ፤ ሌላ የተለየ ነገር የለውም፡፡”

” ካለፈው ስህተታችን ልንማር ይገባል” ሳሙኤል ታዬ

ስለዝግጅት

“ዝግጅት ላይ ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡ ፕሪምየር ሊጉ ላይ የነበረን የልምምድ ሁኔታን አስቀጥለነዋል፡፡ በተለየ መልኩ የተዘጋጀንበት ሁኔታ የለም፡፡”

የመከላከያ የሊግ አቋም በነገው ጨዋታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ

“በፕሪምየር ሊጉ ላይ ይህ ያህል ልዩነት ፈጥረን አይደለም አንደኛውን ዙር የጨረስነው፡፡ የተቻለንን ነገር አድርገናል፡፡ በሁለተኛው ዙር የተሻለ ነገር እናመጣለን፡፡ ያው የሚስተካከሉ ነገሮች እንዳሉ ሆነው፡፡”

በኮንፌድሬሽን ዋንጫ በተደጋጋሚ መሳተፍ

“ካለፈው ስህተታችን ልንማር ይገባል ብዬ አስባለው፡፡ ስህተቶቻችንን ወደኋላ ተመልሰን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ስህተቶቻችን አርመን ከካሜሩኑ ቡድን ጋር የሚኖረንን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለብን ብዬ አስባለው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ጠንክረን ህዝቡን ወደ ሜዳ ልናመጣበት የምንችልበትን ጨዋታ መጫወት ብቻ ነው።”

Leave a Reply