“የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጠንክረን እየሰራን ነው” ሻለቃ በለጠ ገብረኪዳን

በቶታል 2017 የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆነው መከላከያ የካሜሮኑን ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚን አዲስ አበባ ላይ ያስተናግዳል፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ ሻለቃ በለጠ ገብረኪዳን ስለቡድናቸው ዝግጅት፣ ወቅታዊ አቋም እና ጉዳት ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ስለዝግጅት

“ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ተዘጋጅተናል ጥሩም እየሰራን ነው፡፡ ውድድር ላይ ነው የነበርነው፡፡ ፕሪምየር ሊጉም እንዳያችሁት አሁን ነው የቆመው ስለዚህም ውድድሩ በራሱ ጥሩ መዘጋጃ ነው፡፡ የተሻለ ነገር ለማምጣት ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡”

ስለዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ

“ተጋጣሚያችንን ባለፈው ነው ለማየት የሞከርነው፡፡ አሁን ላይ ሶስተኛ ደረጃ ያለ  የካሜሩን ቡድን ነው፡፡ እኛም የተሻለ ነገር ለማምጣት ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡”

የጥር ወር የፕሪምየር ሊግ አቋም በኮንፌድሬሽኑ ዋንጫ ላይ ያለው ተፅዕኖ

“ቡድናችን ባሳለፍነው ታህሳስ (የሶከር ኢትዮጵያ) የወሩ ምርጥ 11 ውስጥ ተጫዋቾችን ማካተት ችሏል፡፡ ኮከብ ተጫዋችም ከክለቡ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ቡድናችን የመዋዠቅ ችግር አይደለም ያለበት የአጨራረስ ችግር እንጂ፡፡ በቅርቡ እንኳን ከፋሲል ከተማ በጎዶሎ ተጫዋች ተሽለን የወጣንበት ሁኔታ አለ፡፡ በፕሪምየር ሊጉም ወደፊት ተጭኖ የሚጫወት እና ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡ አሁንም የአጨራረስ ችግሮች አሉብን እነሱን ደግሞ በሂደት ይስተካከላል ብለን ነው የምናስበው፡፡ እንደቡድን ግን የአቋም መዋዠቅ እምብዛም አልታየብንም፡፡”

በተደጋጋሚ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ መሳተፍ

“ባለፈው ዓመትም ተወዳድረናል ከዛ በፊትም በኬንያው ሊዮፓርድስ ጋር ተጫውተናል፡፡ ከባለፈው ችግራችን ተነስተን ሃገር ወክለን በመቅረባችን ለተሻለ ነገር እየሰራን ነው፡፡ ምክንያቱም ዓምና መሳተፋችን በስነልቦናው ረገድ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምንም ችግር የለውም፡፡ ጥሩ ውጤት እንድናመጣ የልጆቹም ፍላጎት እንዲሁም ክለቡ እያደረገልን የሚገኘው ድጋፍ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በዚህም አጋጣሚ የእግርኳስ አፍቃሪውም እንዲሁም የሰራዊቱ አባል (የሰራዊቱ አባል ከደሞዙ በደንብ ያግዘናል) ግን ቡድኑን ደግሚ ወደ ሜዳ ገብቶ እንዲደግፍ በዚህ አጋጣሚ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለው፡፡”

ስለጉዳት

“እንዳያችሁት ባዬ ከረጅም ግዜ ጉዳት በኃላ ወደ ጥሩ ነገር እየመጣልን ነው፡፡ ግን እስካሁን በፕሪምየር ሊጉ አልተጫወተም፡፡ ስለዚህም ባዬን ለመጠቀም ረጅም ግዜ ነው የፈጀብን ምክንያቱም ለማገገም ግዜ ወስዶበታል፡፡ አንደኛው ዙር ላይ አልነበረም አሁን ግን በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ግን የጨዋታ ዝግጁነቱ በጨዋታ መታየት አለበት፡፡ አሁን እሱን ወደ ውድድር ማስገባት ጫና ውስጥ መክተት ነው፡፡ ልጁ ለእኛም ለሃገርም መጥቀም አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ጤንነቱ መቅደም አለበት፡፡ ጥሩ መሻሻል አለው ግን ከጨዋታ በመራቁ አሁን ብንጠቀምበት ጉዳት አለው፡፡ ሌላው ምንይሉ ወንድሙ ነው፡፡ እሱም ረጅም ግዜ እየተጎዳ አላገለገለም፡፡እሱ የጉልበት ጉዳት ነው ያለው፡፡ ውድድሩ የውጪ ውድድር ነው ቀላልም አይሆንም ስለዚህም እሱ ላይ ባለው ጉዳት ላይ ጨምረን ሌላ ጉዳት ላይ መጣል አንፈልግም፡፡”

Leave a Reply