በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ሀዋሳን አሸነፈ 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር ሙሉ ለሙሉ ዛሬ በተካሄደ ተስተካካይ ጨዋታ ተጠናቋል፡፡ ወደ ይርጋለም የተጓዘው ሀዋሳ ከተማ በሲዳማ ቡና ተሸንፎ ከመሪው ንግድ ባንክ ያለውን ልዩነት የሚያጠብበትን እድል ሳይጠቀም ቀርቷል፡፡

ጨዋታው ማራኪ የኳስ እንቅስቃሴ ቢኖረውም ሽኩቻና በተደጋጋሚ በሚወድቁ ተጫዋቾች ሲደበዝዝ ተስውሏል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በተነሳሽነት ሲጫወቱም ተስተውሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናወች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተጫወቱ በሚገኙት እማዋይሽ ይመር እና ምህረት ታፈሰ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን በተደጋጋሚ ሲፈጥሩ የተስተዋለ ሲሆን የሀዋሳ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራም ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ስታመክን ታይቷል፡፡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማ ከስንታየው ማቲዎስ ሙከራ ውጭ ተጨማሪ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ኳስ ይዞ በመጫወት ወደ ፊት በመድረስ ፤ ሲዳማዎች ደግም በመከላከል እና መልሶ ማጥቃት የተሻሉ ነበሩ፡፡

በ78ኛው ደቂቃ የሀዋሳ ከተማ ተከላካይ ሰብለ ቶጋ የሲዳማ ተጫዋች ላይ በክርን በመማታቷ በኢንተርናሽናል ዳኛ ፅጌ ሲሳይ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ተሰናብታለች፡፡ ከሶስት 

ደቂቃ በኃላ ተቀይራ የገባቸው ምህረት  ትቅደም የሰራችውን ስተት ተጠቅማ በሲዳማ ቡና በኩል አስደናቂ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው ምህረት ታፈሰ በ80ኛው ደቂቃ ሲዳማ ቡና 3 ነጥብ ያገኘበትን ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡

ሀዋሳ ከተማ በውድድር ዘመኑ ሶስተኛ ሽንፈቱን ሲቀምስ ሲዳማ ቡና ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አስመዝግቧል፡፡

የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የፊታችን የካቲት 11 በ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሚጀምር ይሆናል፡፡ 2ኛው ዙር የሚጀምረው የካቲት 6 ቢሆንም በክለቦች ጥያቄ መሰረት የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተዘለው 11ኛው ሳምንት ይካሄዳል፡፡

የምድብ ሀ የ1ኛ ዙር ሰንጠረዥ

የምድብ ለ የ1ኛ ዙር ሰንጠረዥ

Leave a Reply