” በ2ኛው ዙር ከመጀመርያው በተሻለ ውጤታማ እንሆናለን ” ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ  

ፋሲል ከተማ የከፍተኛ ሊጉ ቻምፒዮን በመሆን ፕሪምየር ሊጉን ከተቀላቀለ በኋላ የሊጉ ድምቀት ሆኗል፡፡ አንደኛውን ዙር 3ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅም በውጤታማነት ጎዳና እየተራመደ ይገኛል፡፡ ዳንኤል መስፍን ከአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ጋር በክለቡ የ1ኛ ዙር አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ያደረገውን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡


ከከፍተኛ ሊግ አድጎ እንደመጣ ቡድን አንደኛ ዙር ላይ ቡድናቹ የነበረውን አቋም እንዴት ትገመግመዋለህ ?

እንደ መጀመርያው ዙር ያስመዘገብነው ውጤት ጥሩ ነው፡፡ ተጫዋቾቹም ባሳዩት ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ ፤ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዚህ ስኬት ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ሆኖም ለውጤታችን ማማር ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረጉት ደጋፊዎቻችን ናቸው። እንደ አንደኛ ዙር በቂ ነው እንጂ ይህ የመጨረሻ አይደለም ፤ ቡድናችን ከዚህ በላይ ይሄዳል ብለን ነው የምናምነው፡፡


ፋሲል ከሜዳው ይልቅ ከሜዳው ውጭ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ በማድረግ ጎል ያስቆጥራል ፣ አሸንፎ ይወጣል። ይህ የማጥቃት አጨዋወት ፍላጎት ከምን የመነጨ ነው?

ፕሪምየር ሊግ መግባታችንን ስናረጋግጥ ቁጭ ብለን ተወያይተን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለብን የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጭ እንቅስቃሴያችን በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በፕሪምየር ሊጉ የተፃፈ ህግ ይመስል ቡድኖች ከሜዳቸው ውጭ ሲጫወቱ አጥቅቶ ከመጫወት ይልቅ መከላከልን ይመርጣሉ፡፡ ሜዳቸው ላይ ሲጫወቱ ግን አጥቅተው ይጫወታሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለእኛ ተመችቶናል ምክንያቱም አጥቅቶ መጫወት ስለምንፈልግ ነፃነት እንድናገኝ ይረዳናል፡፡ ሜዳችን ላይ ሲመጡ በጥብቅ ስለሚከላከሉ ትንሽ የማጥቃት አጨዋወታችን ላይ እንቸገራለን፡፡


ቡድንህ ከተወሰኑ ተጨዋቾች በቀር ቋሚ 11 የለውም፡፡ በየጨዋታው ተጨዋቾች ይቀያየራሉ ፤ ይህ ምን ያህል ቡድንህን ውጤታማ አድርጎታል ብለህ ታስባለህ ?

የማፈራረቅ ልምዳችን ለውጤታችን ጠቅሞናል ብዬ አስባለው፡፡ አንደኛ ተጫዋቾች ሁልጊዜ እንደሚጫወቱ ማወቅ አለባቸው ፤ ሁሉም ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ እፈልጋለው፡፡ ሌላው ከአቅም ጋር ለውጥ የሚደረገው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉ ተጫዋቾች አቅምና ጉልበት የሚያወጡ ስለሆነ እየቀያየርክ ስታጫውት ይህን አቅም ጠብቆ እንዲጫወቱ ያደርጋል። ሌላው በቡድን ህብረትና አንድነት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ተጨዋች የመጫወት እድል አለኝ ብሎ ስለሚያስብ ይህንን ለጥሩ የቡድን መንፈስ ተጠቅመንበታል።


አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ፋሲል በደጋፊ እና በስሜት የሚጫወት እንጂ በእንቅስቃሴው ከሌሎች ቡድን የተሻለ ነገር አላሳየም ይላሉ፡፡ ለዚህ ያለህ ምላሽ ምንድነው?

ሰዎች የተሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ሜዳ ላይ የሚታየው ይህ አይደለም፡፡ በጥሩ ጨዋታ ብልጫ ወስደን ነው አሸንፈን የምንወጣው ፤ አጥቅተን ስንጫወት በስሜት ብቻ አይደለም በብልሀትም ጭምር ነው። የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችን ተጫዋቾቼ ጠንቅቀው ያውቃሉ ስለዚህ በስሜት ሳይሆን በብልሀት እንጫወታለን።


ከአንደኛው ዙር በመነሳት በሁለተኛው ዙር ላይ ምን ለመስራት አስባችኋል፡፡ በቡድኑ ላይ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ?

እኛ በዋናነት አንድኛው ዙር ላይ እንደ ድክመት አየነው የምንለው ውጤት የማስጠበቅ ችግራችንን ነው፡፡ መርተን አሸንፈን መውጣት የምንችላቸውን ጨዋታዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ማጥቃትን ስናስብ ነጥብ መጣታችን ነው። ብዙ ተመልካች ለምን ጨዋታው ሊያልቅ 10 ወይም 5 ደቂቃ ሲቀረው ሰአት አታባክኑም ይሉናል፡፡ ይህ በሊጉ የተለመደ አካሄድ ቢሆንም እኛ ለተመልካች ክብር እንሰጣለን፡፡ አሁንም በሁለተኛው ዙር ላይ ሰአት ማባከን የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ እንዲሁ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት እንቀጥላለን። ነገር ግን ሌሎች ያሉብንን ክፍተቶች ለመሙላት በከፍተኛ ሊጉ የሚገኙ ወጣቶች ፣ አቅም ያላቸው እና የመጫወት እድል ካገኙ ቡድን ሊጠቅሙ የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ሰሞኑን ጨዋታዎችን እየተከታተልኩ ነው ፤ የተወሰኑ ተጫዋቾችን አስፈርማለው፡፡ ከዚህ ባለፈ በውጭ ተጨዋቾች ብዙም ፍላጎት የለንም፡፡

አዳዲስ ተጫዋቾች ሲመጡ ብዙም ግልጋሎት ያልሰጡ ተጫዋቾችን እንቀንሳለን፡፡ የተጫዋቾቻችን የውድድር ዘመኑን እንቅስቃሴ የሚገልጽ ቁጥራዊ መረጃ አለን፡፡ ይህን ተንተርሰን ተጨዋቾች የምንቀንስ ይሆናል፡፡

Leave a Reply