” በ2ኛው ዙር ስኬት ለማስመዝገብና ዋንጫ ለማንሳት ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን” ሽመክት ጉግሳ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር ድንቅ ከቋማቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች አንዱ የደደቢቱ የመስመር አጥቂ ሽመክት ጉግሳ ነው፡፡ ሰማያዊዎቹ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው 1ኛውን ዙር እንዲያጠናቀቅቁም የሽመክት ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ ሽመክት ጉግሳ በወቅታዊ አቋሙ እና ተያያዥ ጉዳየዮች ዙርያ ከሚልኪያስ አበራ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡

ደደቢት ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍክ ትገኛለ፡፡ ቆይታህን እንዴት ትገልጸዋለህ?

ወደ ደደቢት ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ በጣም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለው፡፡ ምንም እንኳ ከክለቤ ጋር ዋንጫ ባለማንሳቴ ብቆጭም ባለኝ ቆይታ ደስተኛ ነኝ፡፡ ዘንድሮ ለዋንጫ የምናደርገውን ጉዞ በድል ለማጠናቀቅ ሁላችንም የቡድኑ አባላት እኔም ከመቼውም ጊዜ ጠንክሬ እየሰራው እገኛለው፡፡

በዘንድሮ የውድድር አመት በደደቢት ውጤታማነት ከሚጠቀሱ ቁልፍ ተጨዋቾች አንዱ ነህ…

እንዳያችሁት የዘንድሮ አመት እንቅስቃሴዬ ጥሩ ነው፡፡  ይህ የሆነው ደግሞ የቡድናችን ጥሩ መሆን ነው፡፡ ደደቢት በየቦታቸው የሚጫወቱ ጥሩ አቅም ያላቸው ቁልፍ የሆኑ ተጨዋቾች ያሉበት ስብስብ ነው፡፡  ከጨዋታ ጨዋታ እየጠነከረ እየመጣ ነው ፤ ይህ ደግሞ ለኔ ጥሩ መንቀሳቀስ አግዞኛል፡፡

ከመስመር እየተነሳህ በምታደርገው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ትታወቃለህ፡፡ ይህን እንቅስቃሴ እንዴት አዳበርከው ?

የመስመር አጥቂ ስትሆን አጨዋወትህ ለአጥቂ ኳስ ማሻገር ብቻ ሳይሆን እንደ አጥቂ ሚና ሊኖርህ ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰአት በአለም እግር ኳስ ላይ እንደምናየው በአብዛኛው የመስመር ተጨዋቾች ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በመፍጠር ብቻ ሳይሆን ጎል የማስቆጠር አማራጭ ሆነዋል፡፡ እኛ ጋርም ከመስመር ተነስተን አጥቅተን እንድንጫወት ነው አሰልጣኞቼ ሁሌም የሚነግሩኝ፡፡ ብዙ ወደ ኃላ አላስብም ማለትም ከኋላ ያሉት ልጆች ጥሩ ናቸው፡፡ ያ መሆኑ ደግሞ ብዙ ወደ ማጥቃቱ እንዳመዝን አድርጎኛል፡፡

በሁለተኛው ዙር ለዋንጫ የምታደርጉትን ጉዞ ለማጠናከር  ከአንተ እና ከደደቢት ምን እንጠብቅ?

ቅድም እንዳልኩህ ከደደቢት ጋር ዋንጫ አለማንሳቴ ቁጭት አለብኝ፡፡ በአንደኛው ዙር ጥሩ ጉዞ አድርገናል ፤ አስተውላቹ ከሆነ ነጥብ የጣልንባቸው ጨዋታዎች እየመራን በጥቃቅን ስህተት ነው። አሁን ላይ ቡድናችን ባለበት ጉድለት ላይ ተጨዋቾችን አስመጥቶ አስፈርሟል ፤ ቡድኑም ተጠናክሯል፡፡ በሁለተኛው ዙር ስኬታማ ሆነን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን፡፡

Leave a Reply