የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ፋሲል ከተማ 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ቀናት ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ በዛሬው ፅሁፍም አንደኛውን ዙር በ3ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ፋሲል ከተማ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ ተዳሷል፡፡

የፋሲል የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

የአምናው የከፍተኛ ሊግ ሻምፒዮን እና የዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉ ክስተት ፋሲል ከተማ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና 1-0 በመረታት ነበር። ሆኖም በሀገሪቱ ትልልቅ ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ በተከታታይ ያስመዘገበው ድል የመጀመሪያውን ሽንፈት ያስረሳ እና የሁሉንም እግር ኳስ ተከታታይ ቀልብ እንዲስብ ያደረገው ነበር። የክለቡ አስገራሚ ጉዞም ቀጥሎ በ12ኛው ሳምንት ሳይጠበቅ ሜዳው ላይ በደደቢት 1-0 እስከተረታበት ጨዋታ ድረስ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስት አሸንፎ እና ሶስት አቻ ወጥቶ 12 ነጥቦችን ማሳካት ቻለ። ፋሲል ከተማዎች በፕሪምየር ሊጉ ግማሽ የውድድር አመት ውስጥ ጥሩ ጊዜ አላሳለፉም ከተባለ የደደቢቱን ሽንፈት ጨምሮ በጥር ወር መግቢያ ላይ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት አስተናግደው በሁለቱ አቻ የተለያዩበት አጋጣሚ ነው ሊነሳ የሚችለው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን በመጨረሻው ዙር ጨዋታ አዳማ ከተማን እንዲሁም ከሁለተኛ ሳምንት ተዘዋውሮ በመጣው ጨዋታ ወላይታ ድቻን ጎንደር ላይ አስተናግደው ድል በማድረግ የሊጉን አጋማሽ በአስገራሚ ሁኔታ አጠናቀዋል። የሰበሰቧቸው 26 ነጥቦችም የመጀመሪያውን ዙር የዘንድሮ ውድድር  ፕሪምየር ሊጉን በታሪካቸው ለሁለተኛ ጊዜ የተቀላቀሉትን ፋሲሎች በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሆነው በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲያጠናቁ አድርጓቸዋል ።

 የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

ፋሲል ከተማ  አምና የከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን በሁለቱ ሊጎች መሀል ያለው አጠቃላይ ልዩነት የቡድኑን አቋም ከአምናው ጋር በማወዳደር በቀጥታ ንፅፅር ለመመልከት ከባድ ቢያደርገውም በጥቅሉ ግን ክለቡ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ጨዋታዎችን በድል በመወጣት እስከመጨረሻው ለማሸነፍ የመጣር ባህሪ እንዳለው ማንሳት ይቻላል።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

ከፕሪምየር ሊጉ ሌሎች ክለቦች በተለየ ፋሲል ከተማ ተጨዋቾችን አቀያይሮ በመጠቀም እና በተጋጣሚዎች አጨዋወት ላይ የተመሰረተ ተለዋዋጭ የጨዋታ ዕቅድ ይዞ ወደሜዳ በመግባት አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል። የአሰልጣኝ ዘማርያም ቡድን በብዛት የ 4-3-3ን የቡድን ቅርፅ የሚጠቀም ሲሆን የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያዎች የሆኑት ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች የሚያደርጉት የኋላዮሽ እንቅስቃሴ ቅርፁን ወደ 4-1-4-1 የሚቀይርበት ሁኔታም አለ። በተለይ ቡድኑ ሜዳው ላይ በሚያደርጋቸው እና ኳስን መስርቶ በሚጫወትባቸው አጋጣሚዎች የመሀል ሜዳ የበላይነትም እንዲያግዘው ይመስላል ወደ 4-1-4-1 ያደላል። በነዚህ አጋጣሚዎች በኳስ ቁጥጥር በመብለጥ ከተከላካይ አማካዩ ፊት በሚሰለፉ ሁለት የአጥቂ አማካዮች እና በመስመር አማካዮቹ በመታገዝ አደጋዎችን ይፈጥራል። የኳስ ቁጥጥር በሚወሰድባቸው ጊዜም በራሳቸው ሜዳ ላይ በመቆየት ኳስ በሚነጥቁበት አጋጣሚ በፈጣን የማስጥቃት ሽግግር የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ይታያሉ። ፋሲል የተጋጣሚን የአማካይ እና የኋላ ክፍል በከፍተኛ ጫና ውስጥ በመክተት ኳስን የመቀማት ዘመናዊ አቀራረብ ያለው ቡድን ነው።

 ጠንካራ ጎን
ስለፋሲል የመጀመሪያ ዙር ጉዞ በርካታ ጠንካራ ጎኖችን ማንሳት ይቻላል። ከሁሉም ቅድሚያ መውሰድ የሚገባቸው ግን ደጋፊዎቹ ናቸው። በጎንደር ፋሲለደስ ስታድየም ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ በከተማው እና በስቴድየሙ ውስጥ አስገራሚ የእግር ኳስ መንፈስ የሚፈጥሩት የፋሲል ደጋፊዎች ብዙ ርቀትን አቋርጠው ከቡድኑ ጋር በመጓዝ  ከሜዳው ውጪ ጨዋታዎች ሲኖሩም በብዛት በመገኘት ቡድናቸውን ያበረታታሉ። በዚህም ምክንያት ቀይ እና ነጭ ለባሾቹ የአፄዎቹ ደጋፊዎች ለፋሲል ከተማ ብቻ ሳይሆን ለፕሪምየር ሊጉ አጠቃላይ ድምቀት ሆነዋል።

የአሰልጣኝ ዘማሪያም ቡድን ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የሚኖረው መልክ እጅግ አስገራሚ ነው። እንደተጋጣሚው ባህሪ  የመልሶ ማጥቃትንም ሆነ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመጠቀም አቅዶ ሲገባ የቡድኑ ዋና አላማ ጎሎችን በማስቆጠር እና በማሸነፍ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህም ምክንያት አጠቃላይ ከሰበሰበው ነጥብ 46% የሚሆነውን በተጋጣሚዎቹ ሜዳ ላይ ሲያገኝ 53% የሚሆኑትን ጎሎችም ያስቆጠረው እንዲሁ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ነው።

ወደቡድኑ የሜዳ ላይ እንስቃሴ ስንመጣ በአማካይ በጨዋታ 0.5 ጎል ብቻ የሚያስተናግደውን የተከላካይ መስመሩን ማንሳት የግድ ይላል። ይህ ዝቅተኛ የጎል ማስተናገድ ንፃሬ ከጠንካራው የመሀል ተከላካይ መስመር እና በማጥቃት እና በመከላከሉ ላይ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት መስመር ተከላካዮቹ በተጨማሪ አጠቃላይ የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት የሚገልፅ ነው። ፋሲል ከኳስ ቁጥጥር ውጪ በሚሆንባቸው አጋጣሚዎች የፊት እና የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ በተጋጣሚ ተጨዋቾች ላይ የሚያደርሱት ጫና እና ሰፊ የሜዳ ክልልን በመሸፈን ለተከላካይ ክፍሉ በሚሰጡት ሽፋን የመጣ ጥንካሬም ነው።

በማጥቃት ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት እና በ4-3-3 ቅርፅ ከተከላካይ አማካዩ ፊት የሚሰለፉ የአጥቂ አማካዮች የቦታ አያያዝ ወደመሀል ከልክ በላይ ያልጠበበ እና ወደመስመሮች ያለቅጥ ያተጠጋ መሆኑ ቡድኑ ለሚሰነዝረው የተመጣጠነ ጥቃት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው። ከመስመር አማካዮች ጋር የሚኖራቸውም ግንኙነት የቡድኑ  አስፈሪነት ምንጭ ሲያበዛለት ይታያል።  በተለይ ፋሲል በመልሶ ማጥቃት ለሚፈጥራቸው እድሎች በሁለቱም ሽግግሮች ላይ የአማካይ መስመሩ ፈጣን እንቅስቃሴ ክፍተቶችን ለመድፈንም ሆነ ወደተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ፈጥኖ ለመድረስ የሚያደርገውን ጥረት የተዋጣለት እንዲሆን ያስቻለው ሲሆን ቡድኑ ከተለያየ የመጫወታ ቦታ ላይ ካሉ ተጨዋቾች ጎሎችን ማግኘት መቻሉ ግብ ለማስቆጠር  ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን ረድቶታል። 

 ደካማ ጎን

በጨዋታ ቀናት ከሚኖረው ከፍተኛ ጫና እና ግብ ከማስቆጠር ጉጉት ጋር ተያይዞ የመጣ በሚመስል ሁኔታ የፋሲል ከተማ ቡድን ውስጥ እንደ ድክመት ከሚነሱ ነጥቦች አንዱ በሜዳው በሚያደር ጋቸው ጨዋታዎች ላይ የሚመክኑ ኳሶች ብዛት ነው። ቡድኑ ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ሰባት ግቦችን ነው። ከሰባቱ ጨዋታዎች በአምስቱ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱ የሚሳቱትን ኳሶች ኪሳራ ያካካሰ በመሆኑ እንጂ  ሜዳው ላይ ካስቆጠራቸው ግቦች ቁጥር አናሳነት አንፃር ጎንደር ላይ የሰበሰባቸውን ነጥቦች ለማግኘት ይቸገር ነበር።

የአፄዎቹ ተጨዋቾችን እያፈራረቁ የመጠቀም ዕቅድ ከሚያመጣቸው በረከቶች በብዙ መለኪያዎች እየተጠቀመ እንደሆነ መናገር ቢቻልም አልፎ አልፎ ግን ይህን አካሄድ አብዝቶ መጠቀሙ በተጨዋቾች መሀከል የሚኖረውን እና አብሮ ብዙ ሰዐት በመጫወት የሚመጣውን ውህደት ሲቀንስበት ይታያል። ሌላው የቡድኑ ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ውጤት አስጠብቆ በመውጣቱ ላይ ደክሞ እንዲታይ ያደረገባቸው ጨዋታዎች ናቸው። በተለይም ሜዳው ላይ ሀዋሳ ከተማን እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ መከላከያን በገጠመባቸው ጨዋታዎች ላይ ይህ ችግር ቡድኑ በሁለቱ ጨዋታዎች 4 ነጥቦችን እንዲጥል ምክንያት ሆኗል ።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል ?

ምን አልባት ከከፍተኛ ሊግ ተሳታፊዎች መሀል ተጨዋቾችን ሊያስፈርም እንደሚችል ሲነገር ቢቆይም ፋሲል ከተማ ከመጀመሪያው ዙር መጠናቀቅ በኋላ በተጨዋቾች ዝውውር ላይ እምብዛም ሲሳተፍ አልታየም። የጎንደሩ ክለብ ምንም እንኳን አዲስ አዳጊ ክለብ ቢሆንም እስካሁን ከሰበሰበው ውጤት አንፃር በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ከዚህም አንፃር ክለቡ ተጨማሪ ተጨዋቾችን ቢያስፈርምም ሆነ በነባር ተጨዋቾች ለመቀጠል ቢወስን በሁለተኛውም ዙርም እስካሁን በመጣበት የአጨዋወት መንገድ ቀጥሎ ነጥቦችን ለመሰብሰብ እንደሚጥር መገመት ይቻላል።

የቡድኑ መጀመሪያው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጨዋች ኄኖክ ገምቴሳ

የቀድሞው የአዳማ ከተማ አማካይ ከአምና ጀምሮ የፋሲል ከተማን መለያ ለብሶ በመጫወት ላይ ይገኛል። ኄኖክ ቡድኑ ባደረጋቸው የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች ላይ በአጥቂ አማካይነት ሚና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ተስተውሏል። ለቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በሜዳው ቁመት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ወደመከላከል በሚደረገው ሽግግር ወቅት በታታሪነት ሰፊውን የሜዳ ክፍል አካሎ አጠገቡ ከሚሰለፉ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች ጋር በመግባባት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ሲገባ የቡድኑ የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጨዋች ያደርገዋል።

ለሁለተኛው ዙር ተስፋ የሚጣልበት – ኄኖክ አወቀ

ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፋሲልን የተቀላቀለው ኄኖክ በውድድር ዘመኑ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡ የምርጥ ክህሎት ባለቤት የሆነው ኄኖክ በሁለተኛው ዙር የመጫወት እድል ካገኘ ከመስመር ወደ መሀል እየገባ የሚፈጥራቸው የጎል እድሎች ቡድኑን ሊጠቅሙት ይችላሉ፡፡

Leave a Reply