ሱፐር ካፕ፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ቲፒ ማዜምቤ ዛሬ ይፋለማሉ

በካፍ ሱፐር ካፕ ዛሬ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የዲ.ሪ. ኮንጎውን ቲፒ ማዜምቤን ይገጥማል፡፡ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ እና የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊን የሚያገናኘው ሱፐር ካፑ በፕሬቶሪያ ይካሄዳል፡፡

ሱፐር ካፑ በብዛት በቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ሜዳ ሲካሄድ አንዳንድ ግዜ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊው እንዲሁም ካፍ በሚመርጠው ገለልተኛ ሜዳ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የ2007 ሱፐር ካፕ በገለልተኛ ሜዳ አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ የግብፁ አል አሃሊ የቱኒዚያውን ኤቷል ደ ሳህልን በመለያ ምት 5-4 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወሳል፡፡ የ2017ቱ ሰፐር ካፕ በፕሪቶሪያ ሎፍተስ ቨርስፈልድ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ ሰንዳውንስ በአለም ክለቦች ዋንጫ ያሰቡትን ርቀት መጓዝ ባይችሉም በሃገር ውስጥ ሊግ ፉክክራቸው የተሻለ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ብራዚሎች ባሳለፍነው ሳምንት የሱዌቶ ሃያሉን ኦርላንዶ ፓይሬትስ 6-0 በመረምረም አሁንም የማይቀመሱ መሆነዋቸው አስመስክረዋል፡፡ ሰንዳውንስ በጥር ወር ወደ ፈረንሳዩ ምንፔሌይ ያመራውን የመስመር አማካይ ኪገን ዶሊ ቦታ በፍጥነት መሸፈን አሁን ላይ ቢከብዳቸውም ጠንካራው የመሃል ክፍሉ እና የፊት መስመሩ ለተጋጣሚው ማዜምቤ ከባድ ፈተና ይሆናል፡፡

ቲፒ ማዜምቤ ከኮንፌድሬሽን ዋንጫ ድሉ ማግስት ተጫዋቾች መልቀቁን ተያይዞታል፡፡ ቡድኑ ቁልፍ የሚባሉ አራት ተጫዋቾችን ብቻ በዝውውር መስኮቱ አጥቷል፡፡ ኮትዲቯረዘዊው ሮጀር አሳሌ፣ የዲ.ሪ. ኮንጎው ጆናታን ቦሊንጊ፣ ማርቭል ቦፔ እና ክሪስቲያ ሉዬዳማ በዝውውር መስኮቱ ክለቡን ለቀው ወደ አውሮፓ አቅንተዋል፡፡ ክለቡን ለኮንፌድሬሽን ዋንጫ ባለቤትነት ያበቁት ቤልጄየማዊው አሰልጣኝ ሁበርት ቬሉድ ወደ ቱኒዚያው ኤቷል ደ ሳህል ማቅናታቸው ተከትሎ ክለቡን ተወሰነ ግዜ የቀድሞ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኪዲያዳ ሲያሰለጥን ነበር፡፡ የሉቡምባሺው ክለብ አሁን ላይ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡ ፈረንሳዊው ቴየሪ ፍሮጀር ማዜምቤን እየመሩ በሱፐር ካፑ ይቀርባሉ፡፡

የቻምፒየን ሊግ አሸናፊዎች አብዛኞቹ የሱፐር ካፕ አሸናፊዎች ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በ1992፣ 1997 እና 2011 ብቻ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊዎች የሱፐር ካፑን ክብር አግኝተዋል፡፡ የሱፐር ካፑ አሸናፊ 100000 የአሜሪካ ዶላር ሲያገኝ ተሸናፊው 75ሺህ ዶላር ያገኛል፡፡ የግብፁ አል አሃሊ ስድስት ግዜ ሱፐር ካፑን በማሸነፍ ባለሪከርድ ሲሆን የወቅቱ አሸናፊ ቲፒ ማዜምቤ ነው፡፡

Leave a Reply