ፕሪሚየር ሊግ : በድራማዊ ሁኔታ በተጠናቀቀው ጨዋታ ንግድ ባንክ ከ መከላከያ ነጥብ ተጋርተው ወጡ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታ ንግድ ባንክ እና መከላከያ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረጉት ፍልሚያ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታውን ፈፅመዋል፡፡

መከላከያ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ የሚከላከለውን ይግድ ባንክ የኋላ መስመር ለመስበር የፈጀባቸው 2 ደቂ ብቻ ነበር፡፡ የመስመር አማካዩ ማራኪ ወርቁ በጥሩ ሁኔታ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ጦሩን መሪ አድርጓል፡፡ ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከመጀመርያው ግብ ጋር በሚመሳሰል ሂደት ሙሉአለም ጥላሁን የመከላከያን ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ማራኪ ወርቁ በ32ኛው ደቂቃ መከላከያን 3-0 እንዲመሩ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፎ የመጀመርያው አጋማሽ በመከላከያ 3-0 መሪነት ሲጠናቀቅም ጨዋታው ያበቃለት መስሎ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተሸሽለው የቀረቡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ተደጋጋሚ የገብ ሙከራዎች በማድረግ ከ መከላከያ ተሸለው ሲቀርቡ በመከላከያ በኩል የቸልተኝነት እና ትኩረት ችገር ተስተውሏል፡፡

በ53ኛው ደቂቃ ፊሊፕ ዳውዚ የተገኘችውን የፍፀም ቅጣት ምት ወደ ግብ ቀይሮ ንግድ ባንክን ወደ ጨዋታው ሲመልስ ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ናይጄርያዊው ግብ በማስቆጠር 3-0 ሲመራ የነበረው ንግድ ባንክን ነፍስ ዘርቶበታል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ደግሞ ሲሳይ ቶሊ በግንባሩ በመግጨት ንግድ ባንክን አቻ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ ሁኔታም ግድ ባንክ እስከ 53ኛው ደቂቃ ድረስ 3-0 ሲራ ቆይቶ 3-3 አቻ ለመለያየት በቅቷል፡፡

በጨዋታው 2 ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ፊሊፕ ዳውዚ ለከፍተኛ ግብ አግቢነት ከሃገሩ ልጅ ጋር ተፋጧል፡፡ ፊሊፕ 18 ግቦች ያሉት ሲሆን የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ 19 ገቦች አሉት፡፡

ሊጉ ነገ ሲቀጥል ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልድያን አዲስ አበባ ላይ በ11፡00 ያስተናግዳል፡፡ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ደደቢትን ፣ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ አዳማ ከነማን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ በ9 ሰአት ላይ ይጀምራል፡፡

ረቡእ ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ የሚገኙት ኤሌክትሪክ እና ሙገር በተመሳሳይ 9፡00 ሀዋሳ ከነማ እና ወላይታ ድቻን ሲያስተናግዱ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 11፡30 ላይ ይገጥማል፡፡

ያጋሩ