3 ኢትዮጵያውያን የግብፅ ክለቦችን ሊቀላቀሉ ይችላሉ

 

 

የሳልሃዲን ሰይድ እና ዑመድ ዑክሪ ወኪል የሆነው ግብፃዊው ራህማን መግዲ 3 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወደግብፅ ሊግ ክለቦች እንዲዘዋወሩ እየሰራ መሆኑን በትዊተር አካውንቱ አስታውቋል።

ከእግርኳስ ወኪልነት በተጨማሪ በቴሌቪዥን ተንታኝነት የሚሠራውና የግብፅ ብሔራዊ ቡድን የሚዲያ ሃላፊ የነበረው ራህማን መግዲ ስለተጫዋቾቹ ማንነት ያለው ነገር ባይኖርም የቀድሞው የሐዋሳ ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ሽመልስ በቀለ አንዱ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። ሽመልስ ከሱዳኑ አልሜሪክ ክለብ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ክለብ የሌለው ሲሆን ወደፈለገው ቡድን በነፃ ዝውውር መግባት ይችላል። ይህም ተጫዋቹ ካለው ችሎታ እና ልምድ ጋር ተዳምሮ በግብፅ ክለቦች ተፈላጊ ሊያደርገው ይችላል።

ራህማን መግዲ ከ3ቱ ተጫዋቾች አንዱ የዳሽን ቢራ የተከላካይ አማካይ አስራት መገርሳ እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ ተጫዋቹን ጥሩ ችሎታ ያለው ቢሆንም በእስራኤል ሊግ ለአንድ ወር ያህል በማሳለፉ በሁለቱ ሃገራት መሃል ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ምክኒያት የግብፅ ክለብ ይቀላቀላል ብሎ እንደማይገምት ገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት በግብፅ ፕሪምየር ሊግ እየተጫወተ የሚገኝ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ሳልሃዲን ሰይድ ሲሆን የውድድር ዓመቱ እስኪጠናቀቅም በዋዲ ደግላ ክለብ ሲጫወት ቆይቶ በቀጣዩ ዓመት የ8 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነውን አል አህሊ ይቀላቀላል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ዑመድ ዑክሪ ለኢቲሃድ አሌክሳንድሪያ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ3 ዓመታት ለመጫወት በ500 ሺህ ዶላር ክፍያ መስማማቱ የሚታወስ ነው።

ያጋሩ