የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ምልከታ

በዮናታን ሙሉጌታ


የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ (የፕሪሚየር ለግ ክለቦች ብቻ የተሳተፉበት በመሆኑ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ ነው ውድድሩ የተካሄደው) ፍፃሜውን ባገኘበት ጨዋታ መከላከያ ሀዋሳ ከነማን 2-0 ረቷል፡፡ በዚህም አሸናፊው መከላከያ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ሀገራችንን የሚወክለበትን እድል አግኝቷል፡፡ እኛም ጨዋታውን ከታክቲካዊ ጉዳዮች አንፃር እንደሚከተለው ተመልክተነዋል፡፡

ምንም እንኳን በጨዋታው ሂደት አንዳንድ የቅርፅ ለውጦች የነበሩ ቢሆንም በጨዋታው አብዛኛው ክፍል ላይ በምስሉ እንደምትመለከቱት ሁለቱም ቡድኖች የ4-2-3-1 የሜዳ ላይ አደራደርን ይዘው ወደሜዳ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእግር ኳሱ ላይ በብዛት የሚስተዋለው ይህ የተጨዋቾች አደራደር (Formation) ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እንዲሁም በጨዋታ ሽግግር ጊዜ እንደሽግግሩ ዓይነት ቅርፅን ቀይሮ ማጥቃትንም ሆነ መከላከልንም በተመጠነ ሁኔታ ለመተግበር ያስችላል፡፡ 4-2-3-1 በተለይም በሌሎች አቀራረቦች ላይ በሚወስደው የመሀል ሜዳ የቁጥጥር ብልጫ ኳስን ማንሸራሸርን ለሚወዱ ቡድኖች ተመራጭ ነው፡፡

የመጀመሪያ አጋማሽ

ጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሀዋሳ ከነማ በፈጣን አጫጭር ክብብሎሽ ወደጐል ለመድረስ ሞክረዋል፡፡ በተለይም ይህ እንቅስቃሴ በግራ መስመር በኩል በበረከት ይስሃቅ እና በጋዲሳ መብራቱ አማካይነት እየተተገበረ የነበረ ቢሆንም ብዙ ግን አልዘለቀም፡፡ መከላከያዎች የሀዋሳዎችን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወደራሳቸው የአደጋ ክልል ከመግባቱ በፊት በተለይም በበኃይሉ ግርማ እና በአምበሉ ሚካኤል ደስታ አማካይነት እያቋረጡ ለራሳቸው የማጥቃት ሽግግር ኳሶችን ሲጠቀሙባቸው ነበር፡፡

በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የመከላከያ የማጥቃት አጋጣሚዎች መነሻ የነበሩት የሀዋሳ ተጨዋቾች በመከላከያ ሜዳ አጋማሽ ላይ የሚነጥቋቸው ኳሶች እና ደካማ በነበረው ከማጥቃት ወደ መከላከል ሽግግራቸው ይፈጥረው የነበረው ክፍተት ነው፡፡ ነገር ግን መከላከያም ቢሆን እነዚህን ኳሶች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ይዞ ገብቶ አደጋ የሚፈጥሩ ኳሶችን ለመፍጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ድክመት ተስተውሎባቸዋል፡፡ በሂደትም መከላከያዎች ኳሱን በማንሸራሸር ሦስቱን የሀዋሳ የአጥቂ አማካዮች ወደራሳቸው የሜዳ ክፍል እንዲያፈገፍጉና አብዛኛው የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ በሀዋሳ ሜዳ ላይ እንዲገደብ አድርገዋል፡፡ አብዛኞቹ የማጥቃት ኳሶቻቸው በምንይሉ ወንድሙና በፍሬው ሰለሞን አማካይነት ይፈጠሩም ነበር፡፡ እዚህ ላይ የሀዋሳ ከነማዎች የመከላከል መስመር አለመናበብ ችግር በጉልህ ታይቷል፡፡ በተለይም በ20ኛው ደቂቃ በነጅብ ሳኒ አማካይነት የተሞከረችው ኳስ መነሻ የነበረው የኋላው ክፍሉ ያለመናበብና ያለመረጋጋት ችግር ነበር፡፡

በ31ኛው ደቂቃ በምንይሉ የተገኘችው ጐልም ኳስ መነሻ የነበረው ራሳቸው ሀዋሳዎች በቀኝ በኩል ማለትም በአንተነህ በኩል አስጀምረውት የነበረው ይህ የማጥቃት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ተቋርጦ ሀዋሳዎች ወደመከላከል የሚያደርጉት ሽግግር ሳይጠናቀቅና የመከላከል ቅርፃቸውን ሳይዙ ኳስ የዕለቱ ድንቅ የነበረው ፍሬው ሰለሞን እግር ስር በመገኘቷና እሱም በፍጥነት ለምንይሉ አመቻችቶ በማቀበሉ ምንይሉም በጥሩ አጨራረስ ብቃት ወደጐልነት ቀይሯታል፡፡ በተቀሩትም ደቂቃዎች መከላከያዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በጐል ሙከራ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል፡፡

ሀዋሳዎች በበኩላቸው በአጫጭር ቅበብብሎች ወደ መከላከያ የግብ ክልል መድረስ ሲቸግራቸው አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶችን ለመጣል ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተወሰኑ አጋጣሚዎች ብቻ የመከላከያው ነጂብ ሳኒና የሀዋሳው ደስታ ዮሐንስ ያረጓቸው ከነበሩ ጥረቶች ውጪ እንዳብዛኛው ጊዜ የሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ሚና በመከላከል ላይ ብቻ ተገድቦ ታይቷል፡፡

ሁለተኛ አጋማሽ

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ይልቅ ለአይን የሚስብ እና የተሻሉም የጐል ሙከራዎች የተደረገበት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ቅያሬዎቻቸውን በሙሉ የተጠቀሙበትም ነበር፡፡ በመጀመሪያ መከላከያ ባዩ ገዛኸኝን በሳሙኤል ታዬ ተክቶ አስገብቷል፡፡

የጨዋታው ፍሰት እንደመጀሪያው ግማሽ የቀጠለ ሲሆን መከላከያዎችም የግብ እድሎችን መፍጠር ቀጥለዋል፡፡ በተለይም በሙሉአለም አማካይነት ከቀኝ መስመር የተነሳችው ኳስ ከጉሉ በቅርብ ርቀት በኃይሉ እና ፍሬው በሚያስቆጭ ሁኔታ ተስታለች፡፡ የመከላከያዎች የማጥቃት አጨዋወት በ51ኛው ደቂቃ በጐል ሲታጀብ ሳይታሰብ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የተላከለትንና ኳስ ነበር ፍሬው ሰለሞን ወደግብ የቀየራት፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር ሀዋሳዎች ወደጨዋታው መንፈስም ወደማጥቃቱም የገቡት በተለይ ዳንኤል ደርቤ ግሩም አሰፋን ተክቶ ከገባ በኋላ ሀዋሳዎች የቀኝ መስመሩን ለማጥቃት ሲጠቀሙበት ተስተውለዋል፡፡ በዚህም ሁኔታ ግን የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የነበረው ኳስን በተጋጣሚ የግብ ክልል ላይ ሲደርሱ በአግበቡ የመቀባበል ችግር አልተለያቸውም ነበር፡፡ በዚህም መሀልም ነበር አሁንም መከላከያው ምንይሉ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሀዋሳን ተስፋ የሚያስቆርጥበትን አጋጣሚ ያመከነው፡፡ እዚህ ላይ የሀዋሳ ከነማ ግብ ጠባቂ የዮሐንስ በዛብህ ጥረት መረሳት የለበትም፡፡

ሁለተኛውና ሦስተኛው የሀዋሳ ከነማ ቅያሬዎች ማለትም መስቀሌ መንግሥቱ አጥቂውን አመለ ሚሊኪያስን እንዲሁም አስቻለው ግርማ አንተነህ ተሻገርን ለውጠው የገቡበት አኳኋን የሀዋሳን የማጥቃት አካሄድ ቀይሮታል፡፡

በዚህም መሠረት በረከት ይስሃቅን የፊት አጥቂ አድርገው አስቻለው ፣ ጋዲሳና መስቀሌ ከእሱ ጀርባ በመሆን አንዳንዴም ቦታ እየተቀያየሩ ለማጥቃት ሞክረዋል፡፡ በዚህም አልፎ አልፎ 4-3-3 በሚመስል አቀራረብ የጐል እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በተለይም በረከት ይስሃቅና ዳንኤል ደርቤ የሞከሯቸው ኳሶች በይድነቃቸው አማካይነት ጐል ከመሆን ድነዋል፡፡ በመከላከያ በኩል አልፎ አልፎ የሚገኙ ኳሶችን ወደፊት ይዞ በመሄድ ጫና ቢፈጥሩም በተለይ ሁለተኛውን ጐል ካስቆጠሩ በኋላ በመከላከል ጊዜ 4-5-1 በሚመስል አጨዋወት ሀዋሳዎችን ወደ ጐል እንዳይቀርቡና ብዙ የማግባት አጋጣሚ እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ፍሬው ሰለሞን ግራውን ይዞ እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙ በሳሙኤል ሳሊሶ ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በቀኝ በኩል የሜዳውን ስፋት ለጥጠው ተጫውተዋል፡፡ በዚህም አቋቋም አደገኛ ኳሶችን ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በመላክ አደጋን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

ከዚህም በላይ ግን ከተከላካዮቹ ፊት የነበሩትን በኃይሉና ሚካኤል ከሳሙኤል ታዬ ፣ ፍሬው ሰለሞንና በኋላም ሳሙኤል ሳሊሶ ጥሩ ሽፋን አግኝተዋል፡፡ ቡድኑ ግብ ሳይቆጠርበት ውጤቱን አስጠብቆ እንዲወጣ የመከላከል አደረጃጀታቸው ወሳኝ ነበር፡፡

ነገር ግን በማጥቃቱ ረገድ የተሳኩ ኳሶችን በማመቻቸት እንዲሁም ረጅም ኳሶችን በመጣል በተለይም በሙሉአለም ጥላሁን ተቀይሮ የገባውን የካርሎስ ዳምጠውን ተክለ ሰውነት ለመጠቀምና ጐል ለማስቆጠር ብዙም ጥረት አላደረጉም፡፡

ማ ጠ ቃ ለ ያ

ሀዋሳ ከነማ ምናልባትም በቂ የልምምድ ጊዜ ካለማሳለፉና ከውድድሩም ድንገተኛነት አኳያ የቅንጅትና የመናበብ ችግሮች ታይተውበታል፡፡ በተለይም በተደጋጋሚ የሚቋረጡባቸው የነበሩት የማጥቃት ኳሶች እንዲሁም በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲደርሱ አስተካክሎ ኳስ የማቀበል ስኬታቸው ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመከላከያ በኩል ከተጋጣሚው የተሻለ የተደራጀ አጨዋወት ያሳየ ሲሆን ነገር ግን ያገኙዋቸውን ያለቀላቸው የጐል እድሎችን በመጠቀምና ወደማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ወቅት በተጋጣሚ የመከላከል ቀጠና በፍጥነት ተገኝቶ ያለቀላቸውን የግብ እድሎችን መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩ የተሻለ ነው፡፡

ያጋሩ