ሳላሀዲን ሰዒድ ለፈረሰኞቹ ተስፋን ይዞ መጥቷል

አጀማመራቸው ያላማረላቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአንጋፋው አጥቂያቸው ከጉዳት አገግሞላቸዋል።

ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት በተፈለገው ደረጃ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማገልገል ያልቻለው ሳላሀዲን ሰዒድ በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ በ76ኛው ደቂቃ ሳልሀዲን የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት በጋዲሳ መብራቴ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወቃል።

ለሳምንታት በቂ እረፍት ሲያደርግ የቆየው ሳልሀዲን ሰዒድ ከጉዳቱ አገግሞ ከቡድኑ ጋር ሙሉ ልምምድ ማድረግ ከጀመረ ሦስተኛ ቀኑ ሆኖታል። ምናልባትም የህክምና ቡድኑ እና የአሰልጣኞቹ አባላት የፊታችን እሁድ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በሚያደርጉት የሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ ላይ ይሰለፍ አይሰለፍ የሚለውን ነገር እስከ ጨዋታው መቃረቢያ ድረስ እንደሚወስኑ ሰምተናል።

በውጤት መዋዠቅ ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሊጉ በአምስት ጨዋታ ሁለት ጎሎች ብቻ አስቆጥረው ደካማ የፊት መስመር ካላቸው ቡድኖች ተርታ እንደመሰለፉ የሳላሀዲን መመለስ ለክለቡ እፎይታን የሚፈጥር ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ