ሪፖርት | ቡናማዎቹ ሆሳዕና ላይ የግብ ናዳ አዘነቡ

በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕናን 5-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን በእጅጉ ከፍ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ድሬዳዋ ላይ አቻ ከተለያየው ቡድናቸው ላይ ሁለት ቅያሬዎችን ሲያደርጉ በዚህም ግብጠባቂው በረከት አማረ እንዲሁም የመስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገ/ተንሳይን ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በማስገባት ጀምረዋል። በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በሜዳቸው ከባህርዳር ከተማ አቻ ከተለያየው ቡድን ውስጥ ተከላካዩቹን ትዕግስቱ አበራና ሱራፌል ዳንኤልን እንዲሁም አማካዩ አብዱልሰመድ ዓሊን ዳግም ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት በማካተት ለጨዋታው ቀርበዋል።

አማኑኤል ዮሐንስ ባደረጋት ሙከራ የጀመረው ጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡና ከወትሮው በተለየ በቀደመውን ጨዋታዎች ያሳዩት የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማሳየት የተቸገሩበት ብሎም በቅብብሎች ወቅት በርከት ያሉ ስህተቶችን ሲሰሩ የታየበት ነበር። ነገርግን በዚህ ሂደት ሀዲያዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች በመጠቀም በኩል ሰፊ ክፍተቶች ነበሩባቸው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደካማ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሀዲያዎች በተለይ ሳይጠበቁ በሚያደርጓቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች ጨዋታውን ሳቢነት አላብሰውታል።

በሒደት ቀስ በቀስ ወደ ቡና የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ሀዲያዎች በ17ኛው ደቂቃ ሄኖክ አርፌጮ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ በበረከት አማረ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት የተገኘውን ኳስ አዩብ በቀታ ተቀልብሶ የሞከራትና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሀዲያዎች በ28ኛውና 29ኛው ደቂቄ አፈወርቅ ሀይሉ አክታትሎ በግንባር በመግጨት እንዲሁም አክርሮ በመምታት ያደረጋቸው ሙከራዎችን በበረከት አማረ ሊያድን ችሏል።

እስከ 30ኛው ደቂቃ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ቡናዎች በ30ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻማን ኳስ ገጭቶ ለማውጣት ግቡን ለቆ የወጣው አቤር ኦቮኖን ክፍተት ተመልክቶ አማኑኤል ዮሐንስ የተመለሰውን ኳስ ከግብጠባቂውና ተከላካዮች አናት በላይ በመምታት ቡድኑን መሪ ያደረገች ማራኪ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር ሰከንዶች ልዩነት አቡበከር ናስር በአስደናቂ ፍጥነት የሆሳዕና ተከላካዮችን አታሎ የቡድኑን መሪነት ከፍ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ሆሳዕናዎች በሄኖክ አርፊጮ አማካኝነት ከማእዘን ያሻገሩት ኳስ ተጨራርፎ ሲመለስ ያገኘው ቢስማርክ አፒያ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ለትሞበት ሊወጣ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በሦስት የመሀል ተከላካዮች ጨዋታውን ጀምረው የነበሩት ሆሳዕናዎች አንድ የመሀል ተከላካይ በመቀነስ የመስመር ተጫዋቹ መስቀሉ ለቴቦን በማስገባት ወደ ጨዋታው መመለስን የተለመ ቅያሬ በማድረግ ነበር የጀመሩት። ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ፍፁም ተሻሽለው ነበር የቀረቡት፤ በኳስ ቅብብሎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ያልተቸገሩት ቡናማዎቹ የሀዲያን የግብ ክልል እየተፈራረቁ ሲያስጨንቁ ውለዋል።

በ53ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ እንዳለ ደባልቄ የሞከረውን አቤር ኦቮኖ ሲያድንበት በደቂቃዎች ልዩነት እንዲሁ አቤል ከበደ ከእንዳለ ከበደ የተቀበለውን ያለቀለት ኳስ በድጋሚ አቢር ሊያድንበት ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ሆሳዕናዎች በ57ኛው ደቂቃ መስቀሉ ሌቴቦ ከረጅም ርቀት የሞከረውና በረከት አማረ በአስደናቂ ሁኔታ ካዳነበት ኳስ ውጭ ወደ ግብ ለመድረስ ተቸግረው ተስተውሏል።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ62ኛና 64ኛ ደቂቃ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች ልዩነታቸውን ማስፋት ችለዋል። በቅድሚያ በ62ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ላይ ሱራፌል ዳንኤል በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር ሲያስቆጥር በ64ኛው ደግሞ አቤል ከበደ በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር ልዩነቱን አራት ማድረስ ችሏል።

ከሁለቱ ተከታታይ ግቦች መቆጠር በኋላ ኢትዮጵያ ቡና ጫናቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉም በ3 አጋጣሚዎች ከሆሳዕናው ግብጠባቂ ጋር 1ለ1 ተገናኝተው እንዲሁም በርከት ባሉ አጋጣሚዎች ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝተው በሚያስቆጭ ሁኔታ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በመጨረሻም በጭማሪው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ታደሰ በጥሩ የማጥቃች ሽግግር የመጣውን ኳስ አሥራት ቱንጆ ከግራ የሳጥን ጠርዝ አመቻችቶለት ማስቆጠር ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ ከነበራቸው የበላይነት አንፃር የተገኙት አጋጣሚዎች ተቆጥረው ቢሆን ለሆሳዕናዎች ቀኑ ከዚህ በላይ አስከፊ በሆነ ነበር።

ጨዋታው 5ለ0 መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በሁለት ተከታታይ የሜዳ ላይ ጨዋታዎቹ 9 ግቦችን በማስቆጠር የደጋፊዎቹ የግብ ጥማት በማራስ ሲቀጥል ደረጃውንም ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በአንፃሩ ሆሳዕናዎች እስካሁን በሊጉ ማሸነፍ አልቻሉም፤ በሊጉ ግርጌ ላይም በሁለት ነጥቦች ለመቀም ተገደዋል።

የጨዋታውን ጎሎች በዩቲዩብ ቻነላችን ይመልከቱ 👇


© ሶከር ኢትዮጵያ