ሪፖርት| ወልዋሎ ከሀዋሳ ነጥብ በመጋራት ከመሪነቱ ተንሸራቷል

ከስድስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል መቐለ ላይ የተገናኙት ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ሀዋሳ ከተማ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በመቐለ ከተሸነፈው ስብስብ ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ (ቅጣት)፣ ዓይናለም ኃይለ እና ካርሎስ ዳምጠውን በሠመረ ሀፍታይ፣ ዳዊት ወርቁ እና ጃፋር ደሊል ተክተው ሲገቡ ሀዋሳዎችም በሲዳማ ቡና ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ሀብቴ ከድር ፣ ወንድምአገኝ ማዕረግ ፣ ዘላለም ኢሳይያስ ፣ ብርሀኑ በቀለ ፣ አክሊሉ ተፈራ እና የተሻ ግዛውን በቤሌንጌ ኢኖህ፣ መሳይ ጳውሎስ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ዳንኤል ደርቤ፣ መስፍን ታፈሰ እና ሄኖክ ድልቢ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ወልዋሎዎች በሚያደርጓቸው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሀዋሳዎች የባለሜዳዎቹን የማጥቃት አጨዋወት ለመቋቋም ሲቸገሩ ተስተውለዋል። ወልዋሎዎች ከፈጠሯቸው ዕድሎችም ኢታሙና ኬይሙኔ በሁለት አጋጣሚዎች የሞከራቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም ከፍቃዱ ደነቀ በጥሩ ሁኔታ የሾለከለትን ኳስ መትቶ ቤሊንጌ በጥሩ ሁኔታ የመለስው ተጠቃሽ ነበር። ወልዋሎዎች ጫና በፈጠሩባቸው የመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጪ በጁንያስ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። አጥቂው ከኢታሙና ኬይሙኔ የተቀበለው ኳስ ተጫዋቾች አታሎ በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ነበር ወርቃማውን ዕድል ያመከነው

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም ብልጫ ተወስዶባቸው ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ሀዋሳዎች በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም መስፍን ታፈሰ ከመስመር ገብቶ አክርሮ መቶት ጃፋር ደሊል የመለሰው ኳስ እና ራሱ መስፍን ታፈሰ በተከላካዮች ትኩራት ማጣት ነፃ አቋቋም ሆኖ ያገኘውን ኳስ መቶ ጃፋር ደሊል እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣው ኳስ ሀይቆቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። ብሩክ በየነ ብቻውን አግኝቶ ያመከነው እና ፀጋአብ ዮሐንስ አክርሮ መቶ ጃፋር ደሊል ያዳነበት ኳስም የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የታየበት ነበር። ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ የመስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ጥምረት ለመጠቀም ጥረት ያደረጉት ሀዋሳዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ ወስደው ዕድሎችም ፈጥረዋል። ከነዚህም መስፍን ታፈሰ ከመስመር አታሎ ወደ ሳጥን ገብቶ ከመምታቱ በፊት በጨዋታው በርካታ ወሳኝ ኳሶች ያዳነው ጃፋር ደሊል ወጥቶ ወደ ውጭ ያወጣው ኳስ እና ዳንኤል ደርቤ ከመስመር አሻግሮት መስፍን ታፈሰ መቶ ተከላካዮች የተደረቡት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በረጃጅም በሚሻገሩ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ወልዋሎዎች በተጠቀሰው አጨዋወት ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ፈጥረዋል። ምስጋናው ወልደዮሐንስ አሻምቶት ጁንያስ ናንጂቡ በግንባሩ ገጭቶ ቤሊንጌ እንደምንም ያወጣው ኳስ እና ራምኬል ሎክ ከመስመር አሻምቶት በተመሳሳይ ጁንያስ በግንባሩ የሞከረው ኳስ ከታዩት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ከዚህ ውጭ በተመሳሳይ ከመስመር ተሻግረው ሰመረ ሀፍታይ እና ጁንያስ ናንጂቡ የሞከርዋቸው ሙከራዎችም ቢጫ ለባሾቹ መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ውጤቱን ተከትሎ ቢጫ ለባሾቹ ለተከታታይ አራት ሳምንታት ከያዙት መሪነት ሲወርዱ ሀዋሳዎች ከተከታታይ ሁለት ሽንፈት አገግመው አንድ ነጥብ ይዘው በመውጣት 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ