ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች አርብ ፣ ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነዋል። በስምንቱ ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች በየጨዋታዎቹ ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።

አሰላለፍ 3-5-2


ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን (ድሬዳዋ ከተማ)

በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች በርከት ያሉ ግቦችን ሲያስተናግድ የነበረው ፍሬው በዚህ ሳምንት ቡድኑ 3 ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በተለይ በ90ኛው ደቂቃ ቡድኑ ላይ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት በማዳን እና የሲዳማዎችን ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች በማክሸፍ ድንቅ ሳምንት አሳልፏል።


ተከላካዮች

አዳማ ማሳላቺ (ስሑል ሽረ)

ይህ የስሑል ሽረ ጋናዊ የመሐል ተከላካይ ተጨዋች በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተካቷል። ተጨዋቹ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ጥቅጥቅ ብሎ ለሚከላከለው ቡድኑ የኋላ ደጀን በመሆን ሲንቀሳቀስ ከመታየቱ በተጨማሪ የቡድን አጋሮቹን ሲመራ እና ሲያስተባብር ተስተውሏል።

ወንድሜነህ ደረጀ (ኢትዮጵያ ቡና)

ይህ ባለፈጣን አዕምሮ ተጨዋች በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ተመርጧል። ተጨዋቹ ዋና ተግባሩ ከሆነው የመከላከል ኃላፊነት በተጨማሪ የቡድኑን የማጥቃት ሂደት ከኋላ ሲያስጀምር እና ሲመራ ታይቷል።

ጌቱ ኃይለማርያም (ሰበታ ከተማ)

ይህ ወጣት ተጨዋች በውበቱ አባተ ቡድን ውስጥ የሚሰጠው ኃላፊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮቹ ቡድኑን ለመጥቀም የሚጥረው ጌቱ ቡድኑ ወላይታ ድቻን በረታበት የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል።


አማካዮች

አማኑኤል ዮሐንስ (ኢትዮጵያ ቡና)

ከኳስ ጋር በምቾት የሚጫወተው አማኑኤል ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕና ላይ የጎል ናዳ ሲያዘንብ ቁልፍ ሚና ተወጥቷል። ተጨዋቹ ከኋላ ጀምሮ ኳስ ለመመስረት የሚጥረው ቡድኑ ወደ ማጥቃት ለሚያደርገው ሽግግር ጥሩ ሚና ሲወጣ ተስተውሏል።

አበባየሁ ዮሐንስ (ሲዳማ ቡና)

አበባየሁ ምንም እንኳን ቡድኑ በሜዳው በድሬዳዋ ቢሸነፍም በጨዋታው በግሉ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ እንዲደርስ የራሱን ጥረት ለማድረግ ያልቦዘነው ተጨዋቹ ቡድኑ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን እንዲያደርግ ከመጣሩ በተጨማሪ ለአዲስ ግደይ ጎል ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል ።

አቤል ከበደ (ኢትዮጵያ ቡና)

ለተለያዩ አማራጭ አጨዋወቶች ምቹ የሆነው አቤል በካሳዬ አራጌ ቡድን ውስጥ ከጨዋታ ጨዋታ እየጎላ መጥቷል። በተለይ አላማ ያላቸው የኳስ ንክክዮችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የሚጥረው ተጨዋቹ በጨዋታው አንድ ጎል በማስቆጠር ጥሩ ጊዜን አሳልፏል።

አቡበከር ናስሩ (ኢትዮጵያ ቡና)

ፍጥነቱን ተጠቅሞ በሚያደርጋቸው የመስመር ላይ ሩጫዎች እና ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሰብሮ በመግባት በሚያደርጋቸው ሙከራዎች የሚታወቀው አቡበከር በቅዳሜው ጨዋታ ሁለት ጎሎችን (አንድ በፍፁም ቅጣት ምት) ከማስቆጠሩ በተጨማሪ የቡድኑ ልዩነት ፈጣሪ ነበር።

ኤቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ታታሪው አቤል ቡድኑ መቐለን ሲያሸንፍ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በወረቀት ላይ ከመስመር እንዲነሳ ኃላፊነት ተሰቶት ወደ ሜዳ የገባው ተጨዋቹ በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከጌታነህ እና ሳልሃዲን ጀርባ እንዲሁም አጠገብ በመገኘት የቡድኑን የፊት መስመር ሲመራ ታይቷል። በጨዋታውም ድንቅ ጎል ያስቆጠረው ተጨዋቹ ሳልሃዲን ላስቆጠረው ጎል ጥሩ ኳስ በማመቻቸት ተሳትፎ አድርጓል።


አጥቂዎች

ሳልሃዲን ሰዒድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ከጉዳት የተመለሰው ይህ አንጋፋ ተጨዋች በትላንቱ ጨዋታ ጥሩ ግልጋሎት ሰጥቷል። ተጨዋቹ የቡድኑን መሪነት ያበሰረች ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ጥሩ ውህደት በመፍጠር በተደጋጋሚ በተጋጣሚ የግብ ክልል ተፅእኖውን ሲያሳርፍ ታይቷል።

ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በትላንቱ ጨዋታ አንድ ጎል የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ጌታነህ ጎል እንዲቆጠር እድልን ከማመቻቸት በተጨማሪ ተጨዋቹ ከግዙፉ ላውረንስ ኤድዋርድ እና ከፈጣኑ ተከላካይ አሌክስ ተሰማ ጋር እየታገለ ለቡድኑ ጥሩ አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ተስተውሏል።


ተጠባባቂዎች

ጃፋር ደሊል (ወልዋሎ ዓ/ዩ)
ዐወል መሐመድ (ወልቂጤ ከተማ)
ፈቱዲን ጀማል (ኢትዮጵያ ቡና)
መስዑድ መሐመድ (ሰበታ ከተማ)
በረከት ደስታ (አዳማ ከተማ)
ኦሴይ ማዊሊ (ፋሲል ከነማ)
ሪችሞንድ አዶንጎ (ድሬዳዋ ከተማ)


© ሶከር ኢትዮጵያ